Fana: At a Speed of Life!

ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር 29 ሺህ 909 መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 896 ሺህ 520 ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር 29 ሺህ 909 ተማሪዎች መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የ2014 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ላይ ሪፖርትና ዋና ዋና ግኝቶች በትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ተሰጥቷል።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ የፈተና አሰጣጡ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ እንደነበርና በሁሉም የሚመለከታቸው አካል ርብርብ በስኬት የተጠናቀቀ እንደነበር አንስተዋል።

በፈተና ወቅትም ምንም አይነት ስርቆት ሳይደረግ የተጠናቀቀ ሲሆን አሁን የተለቀቀው ውጤትም በፈተና ወቅት ሲኮርጁ የነበሩ ተማሪዎችን በማውጣት በስርዓቱ የተፈኑ ተማሪዎችን ብቻ ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ ለፈተናው 985 ሺህ 384 ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተፈተኑና ውጤታቸው የተያዘላቸው ተማሪዎች ቁጥር 896 ሺህ 520 መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ውስጥ በፈተናው ተመዝግበው ያልተገኙ 77 ሺህ 98 ተማሪዎች ሲሆኑ 20 ሺህ 170ዎቹ ደግሞ በፈተናው ተገኝተው በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች እንዳይፈተኑ የተደረጉና ፈተናውን ትተው የሄዱ ተማሪዎች ናቸው ብለዋል።

በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት መስክ ከፍተኛ ውጤት 666 መሆኑ ተገልጿል።

ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ብዛት 29 ሺህ 909 ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ተፈታኞች 3 ነጥብ 3 በመቶ ነው ተብሏል።

ሚኒስትሩ ይህ የፈተና ውጤት ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ስርዓተ ያለበትን ደረጃ ያመላከተ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለዚህም ተጠያቂው ከመንግስት ጀምሮ ሁሉም የትምህርት ማህበረሰቡ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ይህን ውጤት ለመቀየር አጠቃላይ ሀገር አቀፍ የትምህር ስርዓቱን ለመቀየር አዲስ ስትራቴጂን ለማዘጋጀት መታቀዱን አስታውቀዋል።

ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደማይቀላቀሉ የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በውጤታቸው መሰረት ተጨማሪ ተማሪዎችን በመቀበል ለቀጣይ ዓመት ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት እንዲያገኙ ይሰራል ነው የተባለው።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.