Fana: At a Speed of Life!

ለሀገር ውስጥ መፈናቀል ዘላቂ መፍትሄዎችን በማፈላለግ በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐርን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የሀገር ውስጥ መፈናቀልን በዘላቂነት ለማስቀረት እየተሰሩ ባሉ ስራዎች እንዲሁም አደጋው ሲከሰት ለመከከል መንግስት እየተገበራቸው ባሉ ስትራቴጂዎች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ ደመቀ መንግስት በሰውሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ የሚመጣን መፈናቀል ለማስቀረት ብሎም አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ጉዳቱን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ችግሩ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄን ለማምጣት የሚረዱ የልማት ስራዎች ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም ተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው የአርብቶ አደር አካባቢዎች የውሃ ፣ የመስኖ ፣ የጤና እና የትምህርት ልማት ስራዎች በስፋት እየተተገበሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ እና ሁሉንም ባለድርሻ ተቋማት የያዘ ምክር ቤት ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ሚኒስትሩ÷ የመንግስት ጥረት ዓለም አቀፍ አጋር አካላት እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐርም በበኩላቸው÷ ተቋማቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄን በመስጠት ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች ሀገራትም በመልካም ተሞክሮነት ሊወሰድ እደሚገባ ልዩ አማካሪው ተናግረዋል።

የመንግስትን ሁሉን አቀፍ ጥረቶች በፋይናንስ እና አቅም ግንባታ መስክ ለመደገፍ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.