Fana: At a Speed of Life!

የጃፓን መንግስት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ማሽነሪዎችን ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2015 የጃፓን መንግስት ለኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የተለየዩ ማሽነሪዎችን ድጋፍ አደረገ፡፡
 
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃው ዘርፍ አቅም ግንባታና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ የሚገኝ መንግስታዊ ተቋም መሆኑ ነው፡፡
 
ኢንስቲትዩቱ በሰው ሃይልና በማቴራል ራሱን ካደራጀበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በመላው የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ከ7 ሺህ 700 በላይ የውሃ ዘርፍ ባለሙያዎች በ25 የስልጠና ዘርፎች ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን መስጠት መቻሉ ተመላክቷል፡፡
 
ተቋሙ በውሃው ዘርፍ አቅምን በመገንባትና በቴክኖሎጂ ሽግግር በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕዩን እውን የሚያደርግ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለውና ለስልጠናና ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ አገልግሎት የሚውል ማሽነሪ ከጃፓን መንግስት ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
 
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ÷ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ላለፉት 25 ዓመታት የውሃውን ዘርፍ አቅም በመገንባት ረገድ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
አስካሁን ባለው ሁኔታም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የውሃ ባለሙያዎች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ቴክኒካል ስልጠና አግኝተው በክልሎች ሰፊ ስራ እየሰሩ መሆናቸውና ይህም የድጋፉ አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
በጃፓን መንግስት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት የተበረከተው የስልጠናና ቁፋሮ ማሽነሪ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑንና ውስጣዊ አቅምን የበለጠ ለማጎልበት ብሎም ቀስ በቀስ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ተወካይ ሞሪሃራ ካቱሱኪ በበኩላቸው÷ጃፓን ለኢትዮጵያ በግብርና፣በግል ዘርፍ ልማት፣ በውሃ እና ሳኒቴሽን፣ በውሃ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት እና ጤናን ጨምሮ ሰፊ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አስርድተዋል፡፡
 
የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታመነ ሀይሉ÷ ተቋማቸው በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት አድረጎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
የተደረገውም የማሽነሪ ድጋፍ አስከ 350 ሜትር ጥልቀት መቆፈር የሚችልና የተግባር ስልጠናውን ውጤታማ ከሚያደርጉት አንዱ እንደሆነ መናገራቸውን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.