Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የመሬት ወረራን ጨምሮ ከ263 ሺህ በላይ የደንብ መተላለፎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 6 ወራት የመሬት ወረራ እና ህገ ወጥ ንግድን ጨምሮ ከ263 ሺህ በላይ የደንብ መተላለፎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በመዲናዋ በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በዚህ መሰረትም በመሬት ወረራ፣በህገ ወጥ ንግድ፣ በአዋኪ ተግባራት፣በህገ ወጥ ማስታወቂያ እና እርድ እንዲሁም ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር መደረጉን አንስተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም በሁሉም ክፍለ ከተሞች 5 ሺህ 641 በወረራ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን በማስመለስ ለሕዝብ ጥቅም ማዋል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ህገ ወጥ ንግድ በሚያከናውኑ 35 ሺህ 154 ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

በመዲናዋ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ አዋኪ ተግባራት በሚፈጽሙ 626 አካላት ላይም እርምጃ መወሰዱን ነው ያስረዱት፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ባልተለመደ መልኩ በትላልቅ ሆቴሎች የተለያዩ አደንዛዥ እጾችን በሚያስጠቅሙ 1 ሺህ 726 አካላት ላይ እርዘምጃ መወሰዱን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ደረጃውን ያልጠበቀ ህገ ወጥ ማስታወቂያ በተለያዩ ቦታዎች በሚለጥፉ እና በሚያስነግሩ ከ204 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

በአጠቃላይ ባለስልጣኑ በግማሽ ዓመቱ የመሬት ወረራ እና ህገ ወጥ ንግድን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ደንብ የተላለፉ 263 ሺህ 907 አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱን ነው ዋና ስራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡

በቀጣይም መሰል የደንብ መተላለፎችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.