Fana: At a Speed of Life!

80 ወንጀል ነክ ጉዳዮችን ተንትኖ ማሠራጨቱን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት የደረሱትን 1 ሺህ 360 አጠራጣሪ ጉዳዮች መነሻ በማድረግ 80 ወንጀል ነክ ጉዳዮችን ለይቶና ተንትኖ ለሚመለከታቸው አካላት ማሠራጨቱን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ተተንትነው የተሠራጩት ጉዳዮች በውስጣቸው በርካታ አጠራጣሪ የወንጀል ሪፖርቶችን የሚይዙ እና በተለያየ የወንጀል ዘርፍ የሚመደቡ መሆናቸውን በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ እንዳለ አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ከፋይናንስ ተቋማት እና ፋይናንስ ነክ ካልሆኑ የተሰየሙ የንግድና ሙያ ሥራዎች የሚቀርቡ ሪፖርቶችን እንዲሁም ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ አገልግሎቱ መረጃዎችን ተንትኖ ለሚመለከታቸው አካላት እያሠራጨ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከደረሱት አጠራጣሪ ሪፖርቶች መካከል ትልቁን ቁጥር የያዙት፥ የሙስና ወንጀል፣ ሕገ ወጥ የሐዋላ አገልግሎት እና ሕገ ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ምንዛሬ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ከታክስ ወንጀሎች፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት እና ከማጭበርበር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንደደረሷቸውም ነው የተናገሩት፡፡

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት እንደ ሀገር በፋይናንስና ከፋይናንስ ውጭ ባሉ ተቋማት ላይ ኪሣራ ሊያስከትሉ የሚችሉ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በመተንተን፣ በማሠራጨት እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አቶ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሌሎች ሀገራት መሰል ተቋማት እና ከዚህ ወንጀል መከላከል ጋር ግንኙነት ካላቸው ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝም ነው የተመላከተው፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.