Fana: At a Speed of Life!

በቱርክ ምክትል የፍትሕ ሚኒስትር የሚመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱርክ ምክትል የፍትሕ ሚኒስትር የሚመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ እና በቱርክ መንግስታት መካከል ያለው የሕግና ፍትሕ የሁለትዮሽ ትብብር በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ውይይት ለማድረግ በቱርክ መንግስት ምክትል የፍትሕ ሚኒስትር ያኩፕ ሞጉል የሚመራ አምስት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ነው በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደረገው፡፡

የልዑካን ቡድኑ ከፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና ከመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው ጋር ተገናኝቶ ተወያይቷል፡፡

ውይይቱም በሁለቱ ሀገራት መካከል በፈረንጆቹ ግንቦት 10 ቀን 2022 የተፈረሙት በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠትና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር የስምምነት ሰነዶች ከየሀገራቱ አንፃር ስልጣኑ ባላቸው አካላት አማካኝነት ፀድቀው ተግባራዊ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

በተመሳሳይ በአቅም ግንባታና በፎረንሲክ ምርመራ ዙሪያ በሁለቱ ሀገራት መካከል በፈረንጆቹ ነሐሴ 2022 የተፈረሙት መግባቢያ ሰነዶች ተግባራዊ እንዲሆኑ መከናወን ስለሚገባቸው ስራዎች እንዲሁም በሌሎች ሕግና ፍትህ ነክ አጀንዳዎች ላይም ውይይት አድርገዋል።

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ አባላት የአንድነት ፓርክ እና የፍትሕ ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤትን ጉብኝተዋል።

በምክክሩ እና በጉብኝቱ ወቅት የቱርክ ምክትል የፍትሕ ሚኒስትሩ የተመራው የቱርክ የልዑካን ቡድን አባላት ፣ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ እና ምክትላቸው ሙስጠፋ ከማል መገኘታቸውን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.