Fana: At a Speed of Life!

ዕድሜ እየጨመረ ቢሄድም የማስታወስ ችሎታን ለማቆየት የሚረዱ 6 መንገዶች

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰዎች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ የማስታወስ ችሎታቸው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡

ይህ ደግሞ በሚመሩት የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር ይስተዋላል፡፡

ጤናማ የሕይወት መርኆዎችን የሚከተሉ በዕድሜ የገፉ ሰዎች በዘር የሚከሰት የመዘንጋት (አልዛይመር) ሕመም ተጠቂ ቢሆኑም እንኳ የማስታወስ ችሎታቸው የመቀነስ ሂደቱ ዘገምተኛ መሆኑን በዘርፉ ላይ የተሠራ ጥናት አመላክቷል፡፡

በዘርፉ ላይ በተሠራ ጥናት የማስታወስ ችሎታ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ተብለው ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የዕድሜ መግፋት እና እሱን ተከትሎ የሚመጣ የመዘንጋት ችግር፣ የማስታዎስ እና የተግባቦት ችግር “ዲሜንሺያ” አብረው ዕድሜ ልክ የሚኖሩ ችግር እና ሰዎች የሚከተሏቸው የአኗኗር ዘይቤዎች ይገኙበታል፡፡

በተለይ ሰዎች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ የማስታወስ ችሎታቸው እንዳይቀንስ የሚከተሉትን ሥድስት መንገዶች እንዲተገብሩ ጥናቱ ምክረ-ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

1. ጤናማ የአመጋገብ ስርአት፦ ፍራፍሬዎች ፣ ዕፅዋት ፣ ዐሣ፣ ሥጋ ፣ ወተት፣ ጨው ፣ ዘይት ፣ ዕንቁላል ፣ ጥራጥሬ ፣ የቅባት እህሎች፣ ለውዝ እና ሻይን ካካተቱ 12 የሚደርሱ የምግብ ዓይነቶች ቢያንስ ሰባት ያኅሉን መመገብን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ይህን ማድረጉ የማስታወስ ችሎታቸው ለረጅም ጊዜ ሳይቀንስ እንዲቆይ ይረዳቸዋል ተብሏል፡፡

2. የማሠላሠል ልምምዶች፦ መፃፍ ፣ ማንበብ፣ ካርታ እና ቼዝን የመሣሠሉ ጫወታዎችን ቢያንስ በሣምንት ሁለት ጊዜ መጫወትም የማስታወስ ችሎታን ለማቆየት እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከዚህ ባለፈም ውስብስብና ፈታኝ ቀመሮችን በመፍታት የዐዕምሮን የማሠላሠል ብቃት ማሳደግም ለዚህ ይረዳል።

3. ተከታታይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት፦ በሣምንት 150 ደቂቃ ያኅል መካከለኛ ክብደት ያላቸውን እንቅስቃሴዎች መሥራት እንዲሁም ለ75 ደቂቃዎች ደግሞ ከበድ ያሉ እንቅስቃሴዎችን መሥራት የማስታወስ ችሎታን ለማቆየት አንዱ መፍትሄ እንደሆነ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

4. ንቁ ማኅበራዊ ተሳትፎ፦ በሣምን ቢያንስ ሁለት ጊዜ በማኅበራዊ ሥብሠባዎች ላይ መሣተፍ ፣ የተለያዩ የድግስ መርሐ-ግብሮችን መታደም፣ ጓደኞችን እና ዘመዶችን መጎብኘት ፣ የጉዞ መርሐ-ግብር ማዘጋጀት እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ሐሳብ መለዋወጥ የማስታወስ ችሎታን ያቆያሉ ተብለው የቀረቡ ሌሎች ተግባራት ናቸው፡፡

5. ሲጋራ አለማጨስ፦ ማጨስ የማስታወስ ችሎታን ከሚጎዱ ነገሮች አንዱ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የማስታወስ ችሎታዎን እንዳያጡ ደግሞ ሲጋራ አያጭሱ ምክራቸው ነው።

6. አልኮል አለመጠጣት፦ ሌላኛው በዐዕምሮ ጤና ላይ እክል የሚፈጥረው ጉዳይ አልኮል መጠጣት መሆኑን ጥናቱን ዋቢ ያደረገው የቲ አር ቲ ዘገባ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.