Fana: At a Speed of Life!

ወላጅ አባቱን በሽጉጥ ተኩሶ የገደለው ግለሰብ በ23 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወላጅ አባቱን በሽጉጥ ተኩሶ የገደለው ነብዩ ዘላለም የተባለ ግለሰብ በ23 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ነብዩ ዘላለም ህዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ቦሌ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ፊት ለፊት ቴዲ ባር አካባቢ ወላጅ አባቱ ሟች ዘላለም ገ/ሚካኤልን በሽጉጥ ጭንቅላታቸውን ሶስት ቦታ ላይ በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረጉ የወንጀል ህግ አንቀጽ 539(1)(ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡

ክርክሩን የመራው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት መሆኑ ተገጿል፡፡

ተከሳሹ ክሱ በችሎት ተነቦለት ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ተጠይቆ ክዶ የተከራከረ ቢሆንም ዐቃቤ ህግ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ በበቂ ማስረጃ በማረጋገጡ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በተከሳሹ ላይ በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት በ22 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣና ከማህበራዊ አገልግሎት ለ5 ዓመት እንዲታገድ ሲል ወስኖበታል፡፡

በተጨማሪም ÷ውሳኔው ከተሰጠ በኋላ ተከሳሽ ዳኞችን በችሎት ፊት “ውሳኔያችሁ የማይረባ ነው ከተፈታሁ በኋላ አሳያችኋለሁ”በማለቱ በችሎት መድፈር በ1 ዓመት ቀላል እስራት መቀጣቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.