Fana: At a Speed of Life!

የስድስት ወራት አፈጻጸሙ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ተስፋ የሰጠ ነው – ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ስድስት ወራት አፈጻጸም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ሚኒስትሮች ገለጹ።

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል በሆነው ሐላላ ኬላ ተካሂዷል።

ከዘርፎች አፈጻጸም መካከል ግብርና በተለይ ደግሞ በሰብል ልማት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡ ተጠቁሟል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ÷ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችና ተሞክሮዎች ተቀርጸው ወደ ሥራ በመገባቱ ለውጥ መታየቱን ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው÷ በተለይ የኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ አምራች ዘርፉን ማነቃቃቱን ተናግረዋል።

በግማሽ ዓመቱ ስድስት አዳዲስ ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ መግባት መቻላቸውን ጠቁመው÷ በዚህም ከዚህ ቀደም ያልታዩ ገበያዎች ጋር መድረስ መቻሉንም ገልጸዋል።

ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት በተሰራው ሥራም አንዳንድ ምርቶችን ከመተካት ባለፈም ወደ ውጪ መላክ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው÷በግማሽ ዓመቱ የትምህርት ሥርዓቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት ውጤት የተገኘበት እንደነበር ገልጸዋል።

በቀጣይም ከችግሩ በመነሳት ዘለቄታዊ መፍትሄን ለማስቀመጥ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ጠንካራ ሥራ በመሰራት ላይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ÷የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ናቸው፡፡

በስድስት ወራትም 100 ሺህ ቤቶችን በግል ሴክተሩ አስተባባሪነት ለመገንባት ታቅዶ 80 ሺህ ቤቶች መሥራት መቻሉን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.