Fana: At a Speed of Life!

ኤንዞ ፈርናንዴዝ የፕሪሚየር ሊጉ ውዱ ፈራሚ ሲሆን ማንቼስተር ዩናይትድ እና አርሰናል አማካይ አስፈርመዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች በጥር ወር የመጨረሻ ሰአታት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።

የእንግሊዙ ቼልሲ በ107 ሚሊየን ፓውንድ የቤኔፊካውን ኤንዞ ፈርናንዴዝ አስፈርሟል፡፡

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ የ22 አመቱን አርጀንቲናዊ ለማስፈረም ለወራት ድርድር ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ትናንት ምሽት የተጫዋቹ ዝውውር ተጠናቋል፡፡

ኤንዞ ፈረናንዴዝ ወደ እንግሊዝ የመጣበት የዝውውር ዋጋ የፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ቀደም ሲል ጃክ ግሪሊሽ በ100 ሚሊየን ፓውንድ ከአስቶንቪላ ማንቼስተር ሲቲ ያደረገው ዝውውር የፕሪሚየርሊጉ ከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በጥር የዝውውር መስኮት 5 ተጫዋቾችን ያስፈረመው ቼልሲ በጥር የዝውውር መስኮት ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ቀዳሚው ክለብ ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል ማንቼስተር ዩናይትድ ማርሴል ሳቢትዘርን ከባየርን ሙኒክ በውሰት ውል ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል።

ተጫዋቹ ከዝውውሩ በኋላ “ለክለቡ ብዙ ጉልበት እና ልምድ እንደማበረክት ይሰማኛል” ሲል ሃሳቡን ሰጥቷል።

የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ጣሊያናዊውን አማካይ ጆርጊንሆን ከምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ አስፈርሟል።

ማት ዶኸርቲን ለአትሌቲኮ ማድሪድ በነጻ ዝውውር የለቀቀው ሌላኛው የሰሜን ለንደን ክለብ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ፔድሮ ፖሮን ከስፖርቲንግ ሊዝበን የግሉ አድርጓል።

የማንቼስተር ሲቲው ተከላካይ ጆኣኦ ካንሴሎ ሳይጠበቅ የባቫሪያኑን ክለብ በውሰት ውል ሲቀላቀል፥ በርካታ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የቆየው ኖቲንግሃም ፎረስት ጆንጆ ሼልቪን ከኒውካስትል እንዲሁም ኬለር ናቫስን ከፒ ኤስ ጂ አስፈርሟል።

ሳውዝ ሃምፕተን ማልዲኒ ሱሌማናን፣ ሌስተር ሲቲ ሀሪ ሱታርን ከስቶክ ሲቲ እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ሳሚ ሎኮንጋን ከአርሰናል አስፈርመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.