Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ በምግብ እህል አቅርቦት ላይ እክል እንዳይፈጥር በትኩረት እየተሰራ ነው – የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በምግብ እህል አቅርቦት ላይ እክል እንዳይፈጥር በትኩረት እየተሰራ  መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ፥ በግብርናው መስክ የተሰማሩ ሁሉም አካላት ቫይርሱን በመከላከል ረገድ ድርብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

የግብርና ሚንስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፥ የኮሮና ቫይረስን እና የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ በምርት እና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ስጋትን  መደቀኑን አንስተዋል።

በተለይም ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ተጋላጭነት የመለየት ስራና በቫይረሱ ምክንያት የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ነው ሚንስትሩ በመግለጫቸው ያነሱት።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለበልግ እና ለ2ኛ ዙር የመስኖ ስራው የሚያስፈልገውን ግብአት ማቅረብ፣ የበረሃ አንበጣን የመከላከሉ ስራን እንዲሁም በምርት ጉድለት ከውጪ የሚገባ ስንዴ ማስገባት ላይ ችግሮች መኖራቸውም ተነስቷል።

ይህንን ችግር ለመፍታትም 69 ሺህ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጥ እና የመከላከል ስራ ላይ ተሰማርተዋልም ብለዋል አቶ አመር።

አያይዘውም  አርሶ አደሩ ለገበያ የሚቀርብ ምርት ላይ  እጥረት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ምርቱን ማቅረብ ይኖርበታል ብለዋል።

በልማታዊ ሴፍቲኔት እና በሌሎች ማእቀፎች ታቅፈው የሚገኙ ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ስራቸው ቢስተጓጎልም ክፍያቸው ግን አይቋረጥምም ነው ያሉት።

የበረሃ እንበጣ ያደረሰውን ጉዳት በመጀሪያ ዙር በተደረገ ጥናት 200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፥ በ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርትም ማሳጣቱም ተገልጿል።

በዙፋን ካሳሁን እና ምስክር ስናፍቅ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.