Fana: At a Speed of Life!

ኢጋድ በቀጣናው አደጋ በመመከት የጎላ አበርክቶ ማድረጉን ዋና ፀሀፊው ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት /ኢጋድ/ በቀጣናው የተከሰተውን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ በመመከት የጎላ አበርክቶ ማድረጉን የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ፡፡

ኢጋድ በቀጣናው ያከናወናቸውን ተግባራት አስልክቶ 3ኛውን ዓመታዊ ሪፖርት በኬንያ ሞምባሳ እየገመገመ ነው፡፡

በዚሁ ወቅት ወርቅነህ ገበየሁ ባደረጉት ንግግር÷ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት የኢጋድ ቀጣና ያለውን ሰፊ የፖለቲካ ፍላጎትና ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ፣ የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭትን ለማስቆም የተሠሩ ሥራዎችን በአብነት አንስተዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን የሚካሄደውን ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ የምክክር ሂደት ለመደገፍ የኢጋድን ሚና፣ በሶማሊያ ለማረጋጋት እየተደረገ ያለውን ጥረት እና ከአልሸባብ አሸባሪ ቡድን ጋር የሚደረገውን ትግልም አንስተዋል ዋና ጸሐፊው፡፡

አሁንም በሠላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ላይ ተጽእኖ ያላቸው ቀጣናውን የሚነኩ ግጭቶችን ዘርዝረዋል፡፡

ኢጋድ ለዓለም አቀፍ ወረርሽኝ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ለቀጣይ ድርቅ፣ ለአንበጣ መንጋ እና ወቅታዊ የጎርፍ አደጋ ለቀጣናዊው የምግብ ዋስትና ችግር የሰጠውን ምላሽም አብራርተዋል፡፡

የቀጣናውን ውህደት ለማፋጠን እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለአካባቢው ያለውን ከፍተኛ አቅም ለማሳደግ ኢጋድ ቁርጠኛ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ለኢጋድ ቀጣና አስተማማኝ የሰላም መንገድ በቀጣናዊ ውህደትና አንድነት÷ እድገትና ብልፅግናን ማስፈን መሆኑን ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል፡፡ #Ethiopia

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.