Fana: At a Speed of Life!

ከባሕላዊ ዕሴቶቻችን መላላት የሚመነጨው የፖለቲካ ስብራት ያለፉት 4 ዓመታት ውጤት አይደለም – ዶ/ር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አክራሪነት፣ ፅንፈኝነትና ከባሕላዊ ዕሴቶቻችን መላላት የሚመነጨው የፖለቲካ ስብራት ብዙዎች እንደሚያስቡት ያለፉት አራት ዓመታት ውጤት አለመሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በተሳሳተ ትርክት ላይ ተመስርቶ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ባለፉት አሥርት ዓመታት በኢትዮጵያዊነት ማንነት እና ብሔርተኝነት ላይ መዘራቱን፤ እነሱን ለማስታገስ ሥራ ላይ የነበረው የአፈና ሥርዓት ያስከተለው ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዛሬ የሚስተዋሉ ጉዳዮች አዲሱ አካተች የዲሞክራሲ ሥርዓት ሁሉንም ነገር ግልጥልጥ በማድረጉ ነፃነትን በአግባቡ ማጣጣም ካለመቻል የመነጨ ነውም ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱም የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ሂደትና በዚህ ረገድ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውድቀት ውጤት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ባለፉት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ በኮሜርሻል ሕግ የተበደረችው የገንዘብ መጠን የዛሬ አራት ዓመት የጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት 60 በመቶ በላይ ደርሶ ነበር ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

የለውጥ አመራሩ መንግስቱን በተረከበ ማግስት አዳዲስ ብድሮች አግኝቶ ምርታማነትን በማሳደግ የሥራ አጥነት ችግር እንዳይቀረፍም ይህ ችግር እንቅፋት መሆኑን ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ተሸፍኖ ላለፉት 20 ዓመታት ሕዝቡን ምሬት ውስጥ እንደከተተው ቀጥሏልም ነው ያሉት፡፡

ከሰሞኑ በ2015 የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ያስተዋልነውም ይህንኑ ችግር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አሥርት ዓመታት የትምህርት ሥርዓቱና ፖለሲው፣ ከመምህራን አሰለጣጠንና ስምሪት፣ ከነበረው የምዘና ሥርዓት፣ ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ ተማሪዎቹ ያለፉበት የትምህርት ሥርዓትና ሂደቱ ችግሮች ጋር የሚተሳሰር መሆኑን አመላተዋል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች የዛሬ ስብራት ሳይሆኑ ለዘመናት የቆዩና የከረሙ ችግሮች መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።

መንግስት የነዚህን ችግሮች ሥረ-መሠረት በሚገባ አጢኖ፣ አፈታቱ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ተገንዝቦ፣ ብቁ የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጦ መላውን ሕዝብ በሳተፈ አግባብ በዘላቂነት ችግሮቹን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከሁሉም የሚጠበቀው እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በሰከነ መንገድ መረዳት፣ የሚወሰዱ እርምጃዎችን መደጋገፍና የመፍትሄ አካል መሆን ነው ሲሉ አመላክተዋል፡፡

ችግሮቹን ይበልጥ ከማራገብ፣ ከማወሳሰብ፣ በሰከነና መርህን በጠበቀ አኳኋን አንዱ የሌላውን ቁስል በመረዳት፣ በይቅር ባይነት፣ በመቻቻልና በሰጥቶ መቀበል መርኅ በወንድማማችነት መንፈስ ለመፍታት በጋራ መቆም ይገባል ሲሉም ነው ያሳሰቡት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.