Fana: At a Speed of Life!

2ኛው ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ 71 በመቶ መሰራጨቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እየቀረበ ያለው ሁለተኛው ዙር ድጋፍ 71 በመቶ መሰራጨቱን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በዚህም በትግራይ ክልል ለ5 ሚሊየን 202 ሺህ 297፣ በአማራ ክልል ለ2 ሚሊየን 440 ሺህ 767 እንዲሁም በአፋር ክልል ለ715 ሺህ 132 ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እየቀረበ መሆኑ ተገልጿል።

እስካሁን በሁለተኛው ዙር 239 ሺህ 628 ሜትሪክ ቶን ምግብ መከፋፈሉን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ድጋፉን የሚያቀርቡት፥ መንግሥት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት እና ጊዜያዊ ክፍተትን የሚሸፍኑ ሌሎች አጋር አካላት ናቸው ብለዋል።

እነዚህ አካላት ለ8 ሚሊየን 358 ሺህ 196 ሰዎች ድጋፍ እያቀረቡ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ድጋፉ ምግብ፣ አልሚ ምግብ፣ መድኃኒት፣ የመጠለያ እና የትምህርት ቁሳቁስ፣ የውኃና የግል ንጽህና መጠበቂያ፣ የግብርና ግብዓት እንዲሁም ነዳጅን ያካተተ ነው ብለዋል አቶ ደበበ።

ድጋፉ በአየር እና በየብስ ትራንስፖርት እየተጓጓዘ ሲሆን፥ ወደ መቀሌና ሽረ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገንዘብ መላኩንም ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት።

1 ሚሊየን 113 ሺህ 961 ሊትር ነዳጅ በ29 አጋር አካላት አማካይነት መቅረቡም ተመላክቷል።

በበልግ ወቅት በተጠናው መሰረት ለ21 ነጥብ 2 ሚሊየን ሕዝብ የዕለት ድጋፍ እየቀረበ ነው ተብሏል።

ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ያክሉ ተፈናቃዮች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

በየጊዜው የሚከሰቱ ሁኔታዎች ቁጥሩን እንደሚጨምሩት ያነሱት አቶ ደበበ፥ ሰላማዊ ሁኔታዎችን ተከትሎ ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ወገኖች እስከሚቋቋሙ ድጋፍ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።

መንግሥት በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ሆኖም በራሱ አቅምና በአጋር አካላት ትብብር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.