Fana: At a Speed of Life!

11ኛው የበጎ ሰው ሽልማት የእጩዎች ጥቆማ የፊታችን የካቲት 1 ቀን ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጎ ሰው ሽልማት 11ኛው መርሐግብር የእጩዎች ጥቆማ ከየካቲት 1 ቀን እስከ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ለአንድ ወር የሚካሄድ መሆኑን የበጎ ሰው ሽልማት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ አስራ አንደኛውን የበጎ ሰው ሽልማት የእጩዎች ጥቆማ አሰጣጥ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ለኢትዮጵያ ባላቸው ሙያ፣ ጊዜ፣ እውቀት እና ገንዘብ በጎ የዋሉና ያሰቡ ኢትዮጵያውያን በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ሲሰጥ መቆየቱ በመግለጫው ተመላክቷል።

የበጎ ሰው ሽልማት በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ አባልና ሰብሳቢ አቶ ነፃነት ተስፋዬ፥ ሽልማቱ በመምህርነት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኪነጥበብ (ሥዕል) ፣ በበጎ አድራጎት፣ በስራ ፈጠራ፣ በመንግስታዊ ተቋማት ኃላፊነት፣ ቅርስና ባህልና ቱሪዝም፣ ማህበራዊ ጥናት፣ ሚዲያና ጋዜጠኝነት እንዲሁም ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ትውልደ ኢትዮጵውያን በሚሉት 10 ዘርፎች እውቅና እንሚሰጥ ጠቁመዋል።

የበጎ ሰው ሽልማት ዋነኛ ዓላማ በመገንዘብ እጩዎችን በሚጠቁሙበት ጊዜ የግለሰቦቹን ማንነት፣ የሚገኙበትን አድራሻና ያከናዎኗቸውን በጎ ተግባራት በዝርዝር እንዲያመላክቱም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቋሚዎች ‘ለሽልማቱ ብቁ ናቸው’ የሚሏቸውን እጩዎችም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት፣ በቫይበር፣ በዋትስአፕ ( +2519-77-23-23-23)፣በኢ-ሜል (begosewprize@gmail.com) እና በፖስታ (150035) አድራሻ የአመቱን በጎ ሰው ጥቆማቸውን ማድረስ ይችላሉ ተብሏል።

የጥቆማ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላም የየዘርፎቹን ተሸላሚ እጩዎች ምርጫ የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸው ዳኞች ይከናወናል።

ድርጅቱ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ አምስት የቦርድ አባላቶቹን በአዲስ የቦርድ አባላት ተክቷል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.