Fana: At a Speed of Life!

2 ቅርሶች በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገቡ የዩኔስኮ ጉባዔ እየተጠበቀ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ የሚዳሰስ እና አንድ የማይዳሰስ በድምሩ ሁለት ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ጉባዔ እየተጠበቀ ነው፡፡

በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ቅርሶች ከክልሎች በዩኔስኮ የይመዝገብልኝ ጥያቄዎች መቅረባቸውን እና ከእነዚህ መካከል ወደ ዩኔስኮ የተላኩ እና አሁን ጥናትና ሥነዳ እየተደረገላቸው ያሉ መኖራቸውን በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አንዱዓለም ግርማዬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በሚዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ ለዩኔስኮ የተላከው ‹‹የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓምድር›› ሲሆን÷ ባለፈው ሐምሌ ላይ መታየት የነበረበት ቢሆንም በዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት የድርጅቱ ጉባዔ መራዘሙ ተገልጿል፡፡

ከማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ ደግሞ ለዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ የተላከው ‹‹የሸዋል ዒድ›› መሆኑን ጠቁመው÷ በ2016 ዓ.ም ሕዳር/ታኅሣሥ ላይ ድርጅቱ በሚያካሂደው ጉባዔ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ‹‹የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ›› ሠነዱ ተጠናቆ ለዩኔስኮ ተልኮ በግምገማ ሒደት ላይ ሲሆን፥ የግምገማ ሂደቱ እንዳለቀ ከጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ቀጥሎ ዩኔስኮ የምዝገባ ውሳኔውን በፈረንጆቹ 2024 ላይ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም የ “መልካ ቁንጡሬና ባልጭት የአርኪዮሎጂካል መካነቅርስ” ሠነድ ተጠናቆ በያዝነው ወር ላይ የተላከና ሌሎችም የሚዳሰሱ ቅርሶች የጥናት ሥራቸው እየተካሄደ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በሶማሌ ማህበረሰብ ዘንድ የሚተገበረው ‹‹ኢሳ ያልተጻፈ ሕግ›› ሠነድ ሥራ እየተጠናቀቀ ስለሆነ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይላካል ነው ያሉት።

የሚዳሰስ ቅርስ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ውድድር የሚበረታበት፣ የሠነድ ዝግጅቱም ከፍተኛ ጊዜ፣ ሀብትና እውቀትን የሚጠይቅ እና በዓመት አንድ ጊዜ ለአንድ ሀገር አንድ ቅርስ ብቻ የሚመዘገብበት መሆኑን እንደፈተና አንስተዋል።

በተጨማሪ ከክልሎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያለማሟላት በዚህም÷ ገንዘብ፣ ጊዜ እና የሰው ኃይል ከወጣባቸው በኋላ ‹የተቀመጡ መመዘኛዎችን አላሟሉም› ተብለው የሚመለሱበት ሁኔታ መኖሩንም ይጠቅሳሉ።

የሚዳሰሱ ቅርሶችን ሠነድ ለማዘጋጀትም ቢያንስ 2 ዓመት እንደሚወስድ ነው የተገለጸው፡፡

የማይዳሰስ ቅርስ የሕዝቦችን ማንነት ከገለጸ፣ የሰብዓዊ መብትን ካልተቃረነ እና ማህበረሰብን በበጎ ካገናኘ÷ ለምዝገባ ተቀባይነት የማግኘቱ ሁኔታ ሰፊ መሆኑ፣ ውድድሩም ከሚዳሰሱ ቅርሶች አኳያ ቀለል ማለቱ እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀሳል፡፡

ነገር ግን በዚህ ዘርፍ ትልቁ ተግዳሮት በዩኔስኮ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ አንድ ቅርስ ብቻ እንዲመዘገብ የሚቀርበው አስገዳጅ ሁኔታ ነው ተብሏል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.