Fana: At a Speed of Life!

የኮኬይን ዕፅ የያዘን የውጭ ሀገር ዜጋ በማስመለጥ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሠረተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ 27 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም ኮኬይን የተሠኘ ዕፅ የያዘ የውጭ ሀገር ዜጋን አስመልጠዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኢንስፔክተሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ አራት ግለሰቦችላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተ፡፡

ክሱ የተመሠረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፌደራል ፖሊስ አባል የሆኑት ተጠርጣሪዎች 1ኛ. ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ ባሌማ እና 2ኛ. ዋና ኢንስፔክተር ጌታነህ ሲሆኑ በተጨማሪም 3ኛ. ተከሳሽ ዳንዔል ተሥፋ የማነ (ሹፌር) እንዲሁም 4ኛው ተከሳሽ የብራዚል ዜግነት ያለው ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ በመባል የሚጠራው ግለሰብ ናቸው።

የፍትኅ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ-ሕግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) ሀ እና (2)ን ተላልፈዋል፡፡

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል ሲሆኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ በቁጥጥር ሥራ ላይ ተመድበው ሲሰሩ ነበር ተብሏል፡፡

ታኅሣሥ 20 ቀን 2015 ከምሽቱ 1 ሠዓት ከ35 ላይ ከብራዚል ሳኦፓሎ ተነስቶ አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ትራንዚት በማድረግ ወደ ጆሃንስቨርግ የሚሄድ ብራዚላዊ ዜግነት ያለውን ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ የሚባል 4ኛ ተከሳሽ “ሴንትራል ጌም” ተብሎ በሚጠራው የፍተሻ ጣቢያ ላይ ሲፈተሽ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከተከለ 27 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ በሻንጣው ውስጥ ይዞ እጅ ከፍንጅ ተገኝቷል፡፡

ይህን ተከትሎም 1ኛ. ተከሳሽ ከሌሎች የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ሠራተኞች ጋር በመሆን ቆሞ ዕፁን አስቆጥሮ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ከእነ ዕፁ 4ኛ.ተከሳሽን በቁጥጥር ሥር አውለዋል፡፡

በመቀጠል 4ኛ ተከሳሽ የሆነውን የውጭ ዜጋ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አደንዛዥ ዕፅ መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የፀረ ፈንጅና አደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር መምሪያ ማስረከብ ሲገባቸው ዕፁንና ግለሰቡን አሳድረው ታኅሣሥ 21 ቀን 2015 ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ10 ላይ 1ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ግለሰቡን ከእነ ዕፁ ጭነው ወደ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ በመውሰድ ላልተያዘ 3ኛ. ተከሳሽ ዕፁንና ግለሰቡን በማስተላለፍ 3ኛ ተከሳሽም በሚያሽከረክረው ኮድ 3_B3 3259 አ.አ በሆነ “ቪትዝ” መኪና ውስጥ በማስገባት አሽሽተዋል ሲል ዐቃቤ ኅግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ጠበቆቻቸው ክሱን ተመልክተው ተዘጋጅተው በክሱ ላይ አስተያየት ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ለፊታችን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.