Fana: At a Speed of Life!

የህጻናት ማንኮራፋት ችግር እና መፍትሄዎቹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የማንኮራፋት ችግር አዋቂዎችም ሆነ ህፃናት ላይ ሊከሰት የሚችል የአተነፋፈስ ችግር ሲሆን፥ አየር ከሳንባ በሚወጣበት እና በሚገባበት ጊዜ በሚያልፍባቸው የአየር ቱቦ በቂ የሆነ ክፍተት ካላገኘ የሚፈጠር ነው።

የህጻናት ስፔሻሊስት እና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ፋሲል መንበረ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ህፃናት ላይ የማንኮራፋት ችግር የሚያስከትሉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ ዋና ዋና ምክንያቶቹ፥

አዴኖይድ የምንለው ከአፍንጫ ውስጥ የሚገኝ የቶንስል ክፍል መጠን መጨመር ወይም ማበጥ፤

በጉሮሮ በግራ እና በቀኝ ከሚገኙ ቶንሲሎች (palatine tonsil) ማበጥ ÷ይህ እብጠት የማንኮራፍት ችግር ከመፍጠሩ በተጨማሪ በተደጋጋሚ የቫይረስ እና የባክቴሪያ ኢንፌክሽን በመያዝ ተጨማሪ የጤና እክል ሊያስከትል የሚችል ነው (ለምሳሌ የልብ እና የኩላሊት ችግሮች)

በአፍና መንገጭላ አካባቢ የሚከሠቱ የአፈጣጠር ችግሮች፣

የአየርና የምግብ የጋራ መተላለፊያ ግድግዳ ችግሮችና (የጡንቻዎች መዛል (የነርቭ ችግሮች)፣ የጉሮሮ በስብ መሞላት፣ ማንኛውም አይነት እባጮች፣ የጉሮሮ መግል መቋጠር እና ማበጥ)

ልማዳዊ ማንኮራፋት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በህጻናት ላይ የሚከሰት የማንኮራፋት ችግር ትኩረት ማጣት እና የመንቀዥቀዥ ችግር፣ አካላዊና አዕምሯዊ የእድገት ውስንነት፣ የሳንባ ከረጢቶች መጠን መቀነስ ፣ የሳንባ ደም ስሮች ግፊት፣ የደም ግፊት መጨመር እና የልብ ህመም ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም ነው የሚናገሩት።

ዶክተር ፋሲል በህጻናት ላይ የሚከሰት የማንኮራፋት ችግር መፍትሄው እንደየምክንያቱ የሚለያይ እንደሆነ ገልጸው÷ ለዚህ ችግር እንደመፍትሄ የሚወሰዱ ህክምናዎች እና መድኃኒቶች አሉት ብለዋል፡፡

የመድሃኒት ሕክምና፣ ቀላል ቀዶ ጥገና ህክምና፣ የኦክስጂን ሕክምና (በተለይ በውፍረት እና በአፈጣጠር ችግር የመጣ ከሆነ)።

የማንኮራፋት ምክንያቱ የቶንስል እና አዴኖይድ ማበጥ ከሆነ በቀላል ቀዶ ጥገና ሕክምና ማስወገዱ ዋናው መፍትሄ ሲሆን ማኮራፋቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንደሚወገድ ነው ዶክተር ፋሲል ያስረዱት፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.