Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 7 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ያለውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ለማሳደግ በ6 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ የተለየዩ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው።

ፕሮጀክቶቹ እየተገነቡ የሚገኙት የውኃ ሽፋኑን ከ81 ወደ 83 በመቶ ለማሳደግ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ተጨማሪ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ነው የተባለው።

የኦሮሚያ ክልል ውና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሐመድ ኑራ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሳደግ በገጠር እና በከተማ 255 ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመንግሥት በጀት እየተገነቡ ነው።

ለዚህም 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።

በቢሮው አማካኝነት 65 ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመው፥ ከዚህ ውስጥ 26ቱን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በዞን ደረጃ እየተገነቡ ከሚገኙት 190 ፕሮጀክቶች መካከል 95ቱን በተያዘው አመት ለመጨረስ እየተሠራ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በህብረተሰቡ ተሳትፎ 7 ሺህ 550 አነስተኛ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ስለመሆኑ አመላክተዋል።

ለእነዚህ ፕሮጀክቶች 2 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ ግንባታቸውን በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ መታሰቡንም ነው የተናገሩት።

በአጠቃላይ በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የክልሉ የንፁህ ውኃ ሽፋን ወደ 83 በመቶ ከፍ እንደሚል ተገልጿል።

የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦቱን ለማሳደግ በሚተገበረው ሥራ ላይ በዋናነት፥ የከርሰ ምድር የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ የሚያከናውኑ ድርጅቶች በታሰበው መጠንና ጊዜ አለመገኘት፣ ብቁ ተቋራጭ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው ጊዜ አለማግኘት የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውም ነው የተመለከተው።

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.