Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ታክሲዎች የተሳፋሪ ቁጥርን በግማሽ እንዲቀንሱ ቢወስንም፤ ትርፍ የሚጭኑና ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አሉ- ተሳፋሪዎች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች የተሳፋሪ ቁጥርን በግማሽ መቀነስ የሚያስችል ውሳኔ በትናንትናው እለት ማሳለፉ ይታወሳል።

ቢሮው በትናንትናው እለት ያሳለፈው የተሳፋሪ ቁጥር መቀነስ እና የታሪፍ ማስተካከያ ውሳኔም በዛሬው እለት ነው መተግበር የተጀመረው።

ሆኖም ግን በትናትናው እለት የወጣውን መመሪያ መተግበር ያልጀመሩ ታክሲዎች መኖራቸው ታውቋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ለመታዘብ እንደቻለው አብዛኛው ተሽከርካሪዎች መመሪያውን መተግበር ቢጀምሩም፤ በአንድአንድ አካባቢዎች ላይ ታክሲዎች ይህንን እንዳልተገበሩ ለመታዘብ ችሏል።

ጣቢያችን ያናገራቸው ተሳፋሪዎችም አልፎ አልፎ ትርፍ የሚጭኑ እና ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ ተመሳሳይ ጥቆማዎች እየደረሱት መሆኑን ነው ያስታወቀው።

የተቀመጠውን መመሪያ የማይተገብሩ አካላት ላይም ከዚህ ቀደም ሲደረግ በተለየ መልኩ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድም ነው ያስታወቀው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በትናንትናው እለት በሰጠው መግለጫ፥ ታክሲዎች ከመደበኛ የመጫን አቅማቸው በግማሽ ቀንሰው እንዲጭኑ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን፥ 12 ሰው የመጫን አቅም ያለው ሚኒባስ ታክሲ 6 ሰው ብቻ እንዲጭኑ መደረጉን መግለፁ ይታወሳል።

ሌሎች ተጨማሪ ወንበር ያላቸው እንደ ዶልፊን ታክሲዎች እንደወንበራቸው አቅም በግማሽ ቀንሰው እንዲጭኑ እና በሃይገር ባስ የተሳፋሪ ቁጥር በወንበር ልኩ በግማሽ ብቻ እንዲጭኑ የተደረገ ሲሆን፥ 14 ሰው ብቻ እንዲጭኑ ውሳኔ ተላልፏል።

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ እና ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አውቶቡሶች 40 ሰው ይጭን የነበረ መደበኛ አውቶቡስ 30 ሰው ብቻ የሚጭኑ ይሆናል።

ከዛሬ ጀምሮም በቀጣይ መመሪያ እስኪሰጥ ድረስ ታክሲም ሆነ ሃይገር አውቶቡስ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት በፊት እና ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጥ መወሰኑም ነው የተገለፀው።

ማንኛውም ከተፈቀደው ሰው በላይ ጭኖና ከተፈቀደው ሰዓት ውጭ ሲሰራ የተገኘ ታክሲም ሆነ የሃይገር አውቶቡስ ብር 5 ሺህ ብር ቅጣት በተጨማሪም የአሽከርካሪው መንጃ ፈቃድ እስከመጨረሻው እንዲታገድ በማድረግ በሌሎች የሀገሪቱ ህጎች ተጠያቂ የሚደረጉም ይሆናል መባሉም ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.