Fana: At a Speed of Life!

ወደ ትግራይ ክልል ለሚጀመረው የየብስ ትራንስፖርት ጉዳት የደረሰባቸው 6 ድልድዮች ተጠግነው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ትግራይ ክልል ዳግም ለሚጀመረው የየብስ ትራንስፖርት በግጭቱ ጉዳት የደሰረባቸው ሁሉም ድልድዮች እና መንገዶች ተጠግነው ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡፡
 
በአስተዳደሩ የድልድይ እና ስትራክቸር ስራዎች ዳይሬክተር ኢንጂነር ጌትነት ዘለቀ እንደገለጹት÷በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ድልድዮችን ጠግኖ አገልግሎት ለማስጀመር አስፈላጊው ርብርብ ተደርጓል፡፡
 
በተለይም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ዳግም ለሚጀመረው የየብስ ትራንስፖርት በግጭቱ ፈርሰው የነበሩ ድልድዮችን በመጠገን ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
 
በዚህ መሰረትም ተከዜ ወንዝ ላይ ለሚገኙ ሁለት ድልድዮች አስፈላጊውን ጥገና በማድረግ ዳግም አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን አንስተዋል፡፡
 
በተጨማሪም አልውሃ፣ጪሬቲ፣ጺላሪ እና ጎቡ ለተሰኙ ድልድዮች አስፈላጊውን ግንባታ በማድረግ ለትራፊክ ክፍት መደረጋቸውን ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
ከስድስቱ ድልድዮች ውስጥ አልውሃ ለሁለተኛ ጊዜ ጥገና የተደረገለት ሲሆን÷የጎቡ ድልድይ ደግሞ እንደ አዲስ የተሰራ መሆኑን አብራተዋል፡፡
 
ከጎቦ ውጪ ያሉት ሌሎች ድልድዮች ፈርሰው የነበሩ እና በላያቸው ላይ ተገጣጣሚ ድልድይ የተገነባላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
ድልድዮችን አስፈላውን ጥገና አድረጎ ዳግም ስራ ለማስጀመርም 173 ነጥብ 17 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አቶ ጌትነት አስረድተዋል፡፡
በሁሉም አቅጣጫ ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ አስፓልት መንገዶችም ለየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል ዳግም የየብስት ትራንስፖር ለመጀመር ሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻ ማህበራት ዝግጁ እንዲሆኑ መመሪያ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.