Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
 
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ግርማ ባይሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ ተማሪዎች በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነው፡፡
 
በተለይም በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
ለዚህም በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን በትምህር ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡
 
አሁን ላይም 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው አቶ ግርማ የገለጹት፡፡
 
በመንግስት ትምህር ቤቶች የሚገኙ ሁሉም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች እና ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
 
በአርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ ቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ጨምሮ በልዩ ሁኔታ ከ1ኛ እስከ 8 ክፍል ያሉ ተማሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
 
በክልሉ በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የተጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስገንዝበዋል፡፡
 
አሁን ላይም በኦሮሚያ ክልል ከ10 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢ ሁኔታ እየተከታተሉ እንደሚገኙ ምክትል ሃላፊው አረጋግጠዋል፡፡
 
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.