Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም “ኢትዮቴል ኢኖቬሽን” የተሰኘ አዲስ ፕሮግራም ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥር የሚያስችል “ኢትዮቴል ኢኖቬሽን” የተባለ አዲስ ፕሮግራም በይፋ አስጀመረ።
 
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ÷ በዛሬው ዕለት በይፋ የተጀመረው አዲስ ፕሮግራም በጀማሪ የክላውድና የሞባይል ፋይናንስ ቢዝነሶች ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
 
ኩባንያው አገልገሎቱን ለማስፋትና ለማዘመን ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ባሻገር ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችና ስራ ፈጠራን ለማበረታታት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
 
የተቀረጸው ፕሮግራም ለጀማሪ የዲጅታልና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ቢዝነስንና ባለሙያዎችን የሚያበረታታ “ኢትዮቴል ኢኖቬሽን” የተባለ አዲስ ፕሮግራም መሆኑንም ነው የተናገሩት።
 
ለፕሮግራሙ ስኬት ኢትዮ ቴሌኮም በቂ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ማከናወኑን የጠቀሱት ስራ አስፈፃሚዋ÷ በዚህም በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።
 
በዚሁ ፕሮግራም በመጀመሪያው ዙር ለ100 ስራ ፈጣሪ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የእድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉም ነው ያሉት።
 
በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለ150 ስራ ፈጣሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እድሉ እንደሚሰጥም ነው የገለጹት።
 
በመሆኑም በ”ኢትዮቴል ኢኖቬሽን” ፕሮግራም የመጀመሪያው ምዕራፍ መወዳደር የሚፈልጉ የክላውድና የሞባይል ፋይናንስ በኢሜል አድራሻ ማመልከት እንደሚችሉ አውስተዋል።
 
በመሆኑም በኤሜል አድራሻ ethiotelinnovation@ethiotelecom.et ከየካቲት 3 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ማመልከት ይችላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ፕሮግራሙ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ያስገነዘቡት ስራ አስፈጻሚዋ ለዚህ ፕሮግራም ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.