Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 550 ሚሊየን ዶላር ማጣቱን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ 550 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማጣቱን ተገለፀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በዛሬው እለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ላይ እያስከተ ባለው ጉዳት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ተወልደ በመግለጫቸውም በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ በቀዳሚነት የአየር መንገድ ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን አንስተዋል።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድም 90 በመቶ የውጭ በረራዉን ቀንሷል ያሉት አቶ ተወልደ፥ ካሉት ከ110 መዳረሻዎች 91 በረራዎችን ቀንሶ በ19 በረራዎች ብቻ እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።

የመንገደኞች የበረራ አገልግሎቱ ቢቀንስም የጭነት (ካርጎ) እገልግሎቱ እና የአውሮፕላን ጥገና ክፍሉ ጥሩ እየሰሩ ነው አመሆኑም አክለው ገልፀዋል።

ሌሎች አየር መንገዶች በሃገራት እየተደጎሙ ነው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ፈተናዉን በራሱ ለመወጣት እየጣረ ነው ብለዋል። አሜሪካ ለአየር መንገድ ዘርፏ የ58 ቢሊየን ዶላር ድጎማ ማድረጉን እንደ አብነት አንስተዋል።

ቋሚ ሰራተኞች ላይ የስራ ቅነሳ ይደረጋል የሚል የተሳሳተ መረጃ በማህበራዊ ድረገፆች መሰራጨቱን የገለፁት አቶ ተወልደ፥ ከቋሚ ሰራተኞች ውጭ ያሉ ሰራተኞች ለጊዜው እንዲያቆሙ አድርገናል ብለዋል።

ቋሚ ሰራተኛ ላይ የተደረገና የታሰበ ቅነሳ እንደሌለም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ከተጓዦች ደህንነት ጋር በተያያዘም፥ ከጉዞ በፊት የጤና ምርመራ እየተደረገላቸው ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው፤ የበረራ ቡድኑ በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት የጤና ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

የበረራ ቡድኑ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንዳልተደረጉ በማንሳትም፤ ራሳቸውን የሚጠረጥሩ ካሉ ግን በአየር መንገዱ የለይቶ ማቆያ ቦታ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ በረራ እያደረገ መሆኑን በማህበራዊ ድረገፆች ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ ነው ያለው አየር መንገዱ ኢሜሬትስ፣ ሉፍታንዛ፣ ኤር ፍራንስ፣ ብሪትሽ ኤር ላይንን ጨምሮ በርካቶች አሁንም በረራ ላይ ናቸው ብለዋል።

የአየር መንገድ ዘርፍ በኮሮናቫይረስ ምክንያት 252 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንደሚያጣ ከዚህ ውስጥ አፍሪካ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ልታጣ እንደምትችል አቶ ተወልደ ገልፀው፤ ከአፍሪካ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ማለታቸውን ዋልታ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.