Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮችና አጋር አካላት የኢትዮጵያን የልማት ስራ እንደሚደግፉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮችና የልማት አጋር አካላት የኢትዮጵያን የልማት እቅድና ስራ እንደሚደግፉ ገለጹ።

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፥ ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድስና የአውሮፓ ህብረት  አምባሳደሮች፣ ከፈረንሳይ የልማት ትብብር ኤጀንሲና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር መክረዋል፡፡

በውይይቱ፥ የግብርናውን ዘርፍ ከማዘመን አኳያ በኩታ ገጠም የግብርና ልማት ስራ ላይ የልማት አጋር አካላት ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል እና አዲስ ተጨማሪ ስራዎችን ማስጀመር እንዲሁም የአሰራር ስርዓትን በማዘጋጀት ተግባራዊነቱን የመከታተል ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም በኢትዮጵያ አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች በክላስተር በማደራጀት ወደ ኢንተርፕራይዝ እንዲያድጉ ለማድረግ ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ እንደሚሰራ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደሮቹና አጋር አካላቱ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ ከዚህ በፊት ያደርጉት የነበረውን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በጦርነትና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምም ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.