Fana: At a Speed of Life!

ከጥቁር ገበያ የሰበሰበውን ዶላር ሕጋዊ አስመስሎ አቅርቧል የተባለው ተከሳሽ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ከጥቁር ገበያ የሰበሰበውን የአሜሪካ ዶላር ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ በመንግስት ላይ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው ተከሳሽ ታደለ ይልማ መኮንን ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ።

ተከሳሹ የብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመሪያ ቁጥር FXD 69/2021 አንቀጽ 7 ቁጥር 7.3.መሰረት ከ3 ሺህ ዶላር በላይ የታሸገ የተፈረመበት የውጭ ምንዛሬ ፎርም ከጉምሩክ ኮሚሽን እንዲያቀርብ የተቀመጠውን የግዴታ አሰራር የፈጸመ በማስመሰል የጉምሩክ አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርጫፍ ሀሰተኛ ዲክላራሲዮኖችን በተጭበረበረ መንገድ አቅርቧል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል።

በፈረንጆቹ 2021 በተለያዩ ቀናቶች ከሀገር ውስጥ ከጥቁር ገበያ የተሰበሰቡ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን ከውጭ ሀገር ያመጣሁት ነው በማለት በወጋገን ባንክ በዳያስፖራ ሒሳብ ውስጥ በማስገባት ወደ ሌሎች ግለሰቦች እንዳዘዋወረ ተገልጿል፡፡

በዚህም በፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በተከሳሹ ላይ 3 ተደራራቢ ክሶችን እንዳቀረበበት ተጠቅሷል፡፡

1ኛው ከባድ የማታለል የሙስና ወንጀል፣ 2ኛ ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መጠቀም የሙስና ወንጀል እንዲሁም 3ኛ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሙስና ወንጀል ክሶች ናቸው።

ተከሳሹ ባለፈው ሳምንት ክሱ እንደደረሰው ተገለጸ ሲሆን÷ዛሬ በነበረው ችሎት ከጠበቃው ጋር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ቀርቦ ጉዳዩ ታይቷል፡፡

ተከሳሹ ውጭ ሀገር ያለኝ የድርጅቴን ጉዳዮች ለማስፈጸም እንዲመቸኝ ባለሁበት አባ ሳሙኤል (ጊዜያዊ ማቆያ) እንድቆይ ይፈቀድልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ወደ ማረሚያ ቤት መውረድ እንዳለበት በማብራራት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በቀረበበት ክስ ላይ የመቃወሚያ መልስ ለመጠባበቅም ለየካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.