Fana: At a Speed of Life!

ለአምራች ኢንዱስትሪው ከሚያስፈልገው 255 ሺህ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እየቀረበ ያለው 68 ሺህ ኪሎ ዋት ብቻ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአምራች ኢንዱስትሪው ከሚያስፈልገው 255 ሺህ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እየቀረበ ያለው 68 ሺህ ኪሎ ዋት ብቻ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዘላቂነት ከኃይል አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያደረገ ነው።

ውይይቱን ያስጀመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ባለፋት ዓመታት የገቢ ምርትን የሚተኩ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማፍራት መቻሉን ገልጸዋል።

ከውጭ ሀገራት ከመጡ ባለሀብቶች መካከልም 60 በመቶ የሚሆኑት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራታቸውንም ጠቁመዋል።

ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የመሰረተ ልማቶች መሟላትና የገበያ እድል መኖር ከውጭ ባለሀብቶች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱም ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በተሰራው ስራ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን እና የኃይል አቅርቦትን ለማሻሻል በተሰራው ስራም አቅርቦቱን 26 በመቶ ማድረስ መቻሉን ነው የገለጹት።

አጠቃላይ አምራች ኢንዱስትሪው የሚያስፈልገው የኃይል አቅርቦት 255 ሺህ ኪሎ ዋት ሲሆን አሁን የቀረበው ግን 68 ሺህ ኪሎ ዋት ነው ብለዋል አቶ መላኩ አለበል፡፡

የኤሌክትሪክ ኬብሎችን እና ትራንስፎርመሮችን በበቂ ሁኔታ በማምረት በሀገር ውስጥ የመተካት ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።

ባለፈው ዓመት 4 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበው የማምረቻው ዘርፍ በዚህ ዓመት ደግሞ በ10 ነጥብ 6 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

በመሳፍንት እያዩ እና በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.