Fana: At a Speed of Life!

ከጣሊያን የእንስሳት የምርምር ማዕከል የመጡ ልዑካን በኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣሊያን ቴራሞ ከሚገኘው (አይ ዜድ ኤስ) የእንስሳት የምርምር ማዕከል የመጡ ልዑካን በሰበታ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ጎብኝተዋል፡፡

በመርሐ-ግብሩ በግብርና ሚኒስቴር የሰበታ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ሩፋኤል÷ የዚህ ጉብኝት ዋና አላማ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከርና ሁለቱን ተቋማት የዓለም አቀፍ የሪፈረንስ ላቦራቶሪ ማዕከል ማድረግ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮና ምክንያት መቆራረጥ ቢኖርም ባለሙያዎችን ወደ ጣሊያን ሀገር ልኮ በማሰልጠንና ከጣሊያን (አይ ዜድ ኤስ) ቴራሞ የእንስሣት ጤና ተመራማሪ ባለሙያዎችን ወደዚህ በመጋበዝ የእውቀት ሽግግር መደረጉን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ልዑካን ቡድኑ ለእንስሳት ጤና ምርምር የሚረዱ እቃዎችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የዓለም የእንስሳት ጤና ምርምር ኤክስፐርት ዶክተር ማሲሞ ሣቺሃ በበኩላቸው፥ በዚህ ስራ አንዱ የበታች ሌላው የበላይ ሆኖ የሚሰራበት ሳይሆን ሁለቱም ተቋማት በአቻነት ተጋግዘው የሚያድጉበት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ የምርምር ማዕከል በርካታ የምርምር ውጤቶች እንደሚጠብቁና ለጣሊያንም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

በዚህ ኢንስቲትዩት የተጀመረው የምርምር ስራ ወደ ጎንደርና መቀሌ በማስፋትና በኔትወርክ በማስተሳሰር በቀጣይ እንደሚሰራ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.