Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በ77 አሜሪካውያን ላይ ማዕቀብ ጣለች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ 33 ከፍተኛ የዴሞክራትና የሪፐብሊካን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ቤተሰቦችን ጨምሮ በ77 አሜሪካውያን ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

ሞስኮ ማዕቀቡን የጣለችው ዋሺንግተን “የሩሲያን ጦር ይረዳሉ” ባለቻቸው 22 ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ከጣለች ከአንድ ሣምንት በኋላ ነው።

በዚህም ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት “አሜሪካ የዩክሬንን ጦር እያገዘች ነው” በሚል ማዕቀቡን የጣለች ሲሆን ፥ እርምጃው ለአሜሪካ የተሰጠ አጻፋዊ ምላሽ ነውም ተብሏል፡፡

ማዕቀብ የተጣለባቸው ግለሰቦችም ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ በቋሚነት የተከለከሉ መሆናቸውን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የአሜሪካ ግዛት አስተዳዳሪ የዴሞክራት እና ሪፐብሊካን የሥራ ኃላፊዎች በማዕቀቡ ከተዘረዘሩ ውስጥ ግማሽ ያህሉን ይይዛሉም ነው የተባለው።

ከእነዚህ ውስጥ የቀድሞዋ የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ ናንሲ ፔሎሲ፣ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት መሪ ቻክ ሹመር እና የሴኔቱ መሪ ሚች ማኮኔል ሴት ልጆች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በሩሲያ ዩክሬን ግጭት ውስጥ በመሳሪያና በከባድ ማሽነሪዎች አቅርቦት ተሳትፈዋል የተባሉ ትላልቅ ኩባንያዎች እና ስራ አስፈጻሚዎቻቸው ላይ ማዕቀብ መጣሉንም ነው የሚኒስቴሩ መግለጫ የሚያመላክተው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ማዕቀቦች የሩሲያ ፖለቲከኞችን፣ ነጋዴዎችን፣ የጦር መሪዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ዒላማ ያደርጉ እንደነበር አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.