Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በፖላንድ የአንድ ማይል ውድድር ሁለተኛውን ፈጣን ሰአት አስመዘገበች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ትናንት ምሽት በፖላንድ ቶረን በተካሄደ የቤት ውስጥ የአንድ ማይል ውድድር የዓለማችን ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፋለች፡፡

አትሌቷ ርቀቱን 4 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ከ16 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ስታጠናቅቅ ይህ ሰዓትም ከገንዘቤ ዲባባ በመቀጠል ሁለተኛው የዓለማችን ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በተመሳሳይ በፖላንድ ኦርለን ኮፐርኒከስ ዋንጫ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

ፍሬወይኒ ሀይሉ 8 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ ከ92 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ቀዳሚ ስትሆን እጅጋየሁ ታዬ 2ኛ፣ ለምለም ሀይሉ 3ኛ እንዲሁም ወርቅውሃ ጌታቸው 4ኛ ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል።

በፈረንሳይ ደ ሞንዴቪል በተካሄደው የ1 ሺህ 500 ሜትር የሴቶች የቤት ውስጥ ውድድር  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ሲያጠናቅቁ  አያል ዳኛቸው 1ኛ፣ ትዕግስት ከተማ 2ኛ፣ ሲንቦ አለማየሁ 3ኛ እንዲሁም ትዕግስት ግርማ 4ኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች አሊ አብዱልመና 7 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ ከ48 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሲያሸንፍ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አብዲሳ ፈይሳ 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ከወርልድ አትሌቲክስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.