Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ተጨማሪ 3 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 225 ሰዎች መካከል 3 ግለሰቦች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር አስታወቀ።

በዚህም በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 55 ከፍ ብሏል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ለ2 ሺህ 496 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል ብለዋል።

በመሆኑም የዛሬዎቹን ሶስት ሰዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 55 ከፍ ብሏል ነው ያሉት።

በ24 ሰዓታት ውስጥ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠው ሶስቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ሁለቱ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች የ29 ዓመት እድሜ ያላቸውና ከዱባይ መጥተው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

አንደኛው ግለሰብ የ36 ዓመት እድሜ ያለውና በአማራ ክልል የአዊ ዞን አዲስ ቅዳምን ከተማ ነዋሪ መሆኑ ነው የተናገሩት።

ግለሰቡ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን÷ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳለው ተጠርጥሮ ምርመራ እንደተደረገበት ተገልጿል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል አንድ ሰው ወደ ጽኑ ህሙማን ማቆያ መግባቱንና ይህም በጽኑ ህሙማን መቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ቁጥር ሁለት እንዳደረሰው ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ባሉበት ክልል በተዘጋጀ የነጻ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።

ህብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግም ነው ያሳሰቡት።

በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል አራቱ ያገገሙ ሲሆን፤ ሁለቱ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። ሌላ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ አገራቸው ተሸኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.