Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ባለሃብቶች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ባለሃብቶች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የክልሉ ምክትል ርዕሠ መሥተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛሆ ዥዩዋንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ኢንጂነር ነጋሽ ÷ የቻይና ባለሃብቶች በተለይም በግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ቢሰማሩ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ክልሉ በወርቅ፣ በድንጋይ ከሰል እንዲሁም በብረት ማዕድን የበለጸገ መሆኑንም ነው ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ የጠቆሙት፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከቻይና እህት ክልሎች ጋር የጠነከረ ግንኙነት የመመስረት ፍላጎት እንዳለው በውይይት ወቅት ተነስቷል፡፡

የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የአጭርና የረጅም ጊዜ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በኤምባሲው በኩል እንዲመቻች ጥያቄ ቀርቧል ።

ክልሉ በቀርከሃ ምርት በስፋት እንደሚታወቅ እና በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ተገልጿል፡፡

አምባሳደር ዛሆ ዥዩዋን በበኩላቸው ÷ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ስራዎች በትብብር እየሰራች እንደሆነ ማንሳታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ክልል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሃብቶች እንዳሉት መረዳታቸውን ጠቁመው÷ይህንንም በቻይና እንደሚያስተዋውቁና የግንኙነት መስመሩን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.