Fana: At a Speed of Life!

በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመው ችግር በሰላማዊ መንገድ ፤ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ፤በስክነትና የቤተክርስቲያኗን ውስጣዊ አሰራር በተከተለ መንገድ እንደሚፈታ የከተማችን አስተዳደር ፅኑ እምነት አለው፡፡

የከተማ አስተዳደራችን በዚሁ ወቅት ያጋጠመውን ችግር አስመልክቶ በቤተክርስቲያኒቱ የታወጀው የፆምና የምህላ ስርዓት በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቀቅ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ሆኖም ግን በከተማችን አዲስ አበባ አዲስ የተሾሙ ጳጳሳትም ሆነ የተሻሩ ጳጳሳት እንደሌሉ እየታወቀ አዲስ የተሾሙ ጳጳሳት ወደቤተክርስቲያን እየመጡ ነው በሚል ሀሰተኛ መረጃ ግጭትና ሁከት ለመቀስቀስ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎችና ማስረጃዎቻችን ያሳያሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የእምነት ጉዳይ ያልሆኑ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ድርጊቶችና ንግግሮችም በስፋት በማሰራጨት በቤተክርስቲያኔ መከፋፈልና መለያየት መኖር የለበትም በሚል በቅንነት አማኙ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወዳልሆነ የትርምስ አቅጣጫ ለመቀየርና ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም መሯሯጥ ይስተዋላል፡፡

በተለይም በተለያዩ ፅንፎች የሚገለፁ አደገኛ መልእክቶችን በታተሙ ወረቀቶችን በተለያዩ ቦታዎች በመለጠፍ ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ መሆኑን፤ እንዲሁም ጉዳዩን ቤተክርስቲያን ለአመፅ እንደጠራች በማስመሰል የክፋታቸውን ልክ የሚገልፁ መልእክቶችን በማህበራዊ ሚድያ በማሰራጨት ለዘመናት ተሳስሮና ተሳስቦ የኖረውን ማህበረሰብ ለመለያየትና እርስ በእርሱ ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዛሬውም እለት በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ አየር ጤና ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አዳዲስ የተሾሙ ጳጳሳት እየመጡ ነው ቤተክርስቲያናችንን ሊነጥቁን ነው በሚል፤ ስልክ ተደውሎ ተነግሮናል በሚል ሀሰተኛ መረጃ ውዥንብር በመፍጠርና ሰዎች ወደ ግጭትና ትርምስ ውስጥ እንዲገቡ ሙከራ ተደርጓል፡፡

ይህም ተግባር በተቀናጀና በተናበበ የሚድያ ዘመቻ ከቤተክርስቲያን ደውል መደወል ጀምሮ በተለያዩ የሚድያ አውታሮች ጉዳዩን ለማቀጣጠልና ይህንንም በመላው ከተማይቱ በሌሎችም ደብሮች በተመሳሳይ መንገድ ለመፈፀም እና ህብረተሰቡን ውዥንብር እና ግጭት ውስጥ ለመክተት ዝግጅት መኖሩን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ግጭት ወደ ትምህርት ቤቶችም ለማስፋፋት የተለያዩ ሙከራዎች መኖራቸውም ምልክቶች ታይተዋል፡፡

ስለሆነም አሁናዊ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያጋጠመው አዳዲስ ጳጳሶች ሹመት በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከትና ደብሮች ውስጥ ያለመሆኑ እየታወቀ ፤ ሆነ ተብሎ ግጭት ለመፍጠር እና የግጭት አውድማውን አዲስ አበባን ለማድረግ የሚደረጉ ጥሪዎች የተሳሳቱ ፤ አግባብነት የሌላቸው ናቸው፡፡

በመሆኑም የከተማችን ነዋሪዎች በአብሮነትና ጠንካራ ተሳትፎ በዘላቂነት ያስቀጠለውን የከተማችንን ሰላም ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ ራሱን ከጥፋት ሃይሎች በመነጠልና ለሁከት ጠሪዎች ምላሽ ባለመስጠት ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በማድረግ የሰላም ባለቤት በመሆን ሃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

አሁንም ቢሆን የከተማ አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያጋጠመውን ችግር በቤተክርስቲያቱ የውስጥ አሰራርና ስርዓት ፤በሰከነ መንገድ እንደምትፈታ እምነታችን ጠንካራ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ የከተማ አስተዳደራችንም ቤተክርስቲያኒቷ ለምታደርገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሁሉ የተለመደውን ድጋፋችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

ይህንን በመተላለፍ በሃይማኖት ሽፋን ዘልቆ የቆየውን የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ወደ ሁከት አውድማነት ለመቀየር የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት የከተማ አስተዳደሩ ፈፅሞ የማይታገስና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ያለበትን ሃላፊነት በመወጣት የህግ የበላይነትን እንደሚረጋግጥና በጥፋት ሃይሎች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አጥብቀን እናሳውቃለን፡፡

ከሰላም እንጂ ከሁከት የሚያተርፍ የለም!!
የካቲት 2/2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.