Fana: At a Speed of Life!

በ5 ዞኖች እና በ1 ልዩ ወረዳ የውጤት ማዳመርና ማመሳከር ሥራ እንደተጠናቀቀ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ይደረጋል- ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ5 ዞኖች እና በ1 ልዩ ወረዳ የውጤት ማዳመርና ማመሳከር ሥራ እንደተጠናቀቀ ጊዜያዊ ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ፡፡

የተዳመረና የተመሳከረ ጊዜያዊ ውጤት በልዩ ወረዳ ደረጃ ይፋ ከተደረገባቸው ውስጥ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ እና ባስኬቶ መሆናቸውን ያሳወቀው ቦርዱ ÷ በዞን ደረጃ ደግሞ በኮንሶ ይፋ መደረጉን ገልጿል፡፡

በቡርጂ ልዩ ወረዳ ውጤት የማዳመር ሥራው በመሰራት ላይ እንደሚገኝ  ቦርዱ አመላክቷል፡፡

በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዲኦና በጎፋ ዞኖች በማስተባበሪያ ማዕከል ደረጃ የማመሳከር ሥራ ተጠናቆ በዞን ደረጃ ለሕዝበ ውሣኔ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች በማስረከብ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በቀጣይም በነዚህ ዞኖች የውጤት ማዳመርና ማመሳከር ሥራው እንደተጠናቀቀ ጊዜያዊ ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጊዜያዊ ውጤት የማዳመርና ማመሳከር ሥራ ከጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም.ባለው ጊዜ እንደተሰራም ተጠቅሷል፡፡

ቦርዱ የሕዝበ ውሣኔውን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ማድረግ መጀመሩንም ነው የጠቀሰው፡፡

በደቡብ ክልል ሥር በሚገኙ 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች ላይ ያካሄደው የሕዝበ ውሣኔ ድምፅ የመስጠት ሂደት መጠናቀቁን ተከትሎ ፤ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ውጤት የማዳመር ሥራው ድምፅ በተሰጠባቸው ጣቢያዎች እንደተከናወነም አሳውቋል፡፡

ዞኖቹ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ እና ልዩ ወረዳዎች ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡

ከሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተሰበሰበውን ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሚያከናወን ይሆናል ተብሏል፡፡

ይህም በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የሚደረገው የመጨረሻ ውጤት የማረጋገጥ ሥራ ሲጠናቀቅ በቦርዱ ፀድቆ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ነው የተባለው።

ቦርዱ በድምፅ መስጫው ቀን በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በመከናወን ላይ የነበረውን ድምፅ የመስጠት ሂደት የጎበኘ ሲሆን ÷ በማዕከል ደረጃም በወላይታና በጨንቻ የተካሄደውን የውጤት ማዳመር ሥራ እንደጎበኘ ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.