Fana: At a Speed of Life!

ለሥራ ወደ ውጪ የሚሄዱ ዜጎች መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሥራ ወደ ውጪ የሚሄዱ ዜጎች መብትና ደህንነታቸው የተጠበቀና የስምሪት ስርዓቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ ከሳውዲ ዓረቢያ አምባሳደር ዶክተር ፋሃድ አባይዳላህ አልሁማየዳኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
ውይይቱ ለሥራ ወደ ሳውዲ ዓረቢያ የሚሄዱ ዜጎች መብትና ደህንነታቸውን ማስጠበቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
ወይዘሮ ሙፈሪሃት÷ከውጭ ስራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የዜጎችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅና ሥራው ከሰው ንክኪ የፀዳና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
ሳውዲ ዓረቢያን ጨምሮ ለሥራ ወደ ውጪ የሚላኩ ዜጎችም ስለሚሄዱበት ሀገር በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ የቋንቋና ሙያዊ ሥልጠና መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
 
የሥራ ስምሪቱ ትኩረት የሠለጠነና በከፊል የሠለጠነ የሰው ሃይል መላክ ላይ እንደሚያተኩር አስገንዝበዋል፡፡
 
አምባሳደር ፋሃድ አባይዳላህ አልሁማየዳኒ በበኩላቸው÷ ሳውዲ ዓረቢያ ከዚህ ቀደም የነበረውን አሰራር በማሻሻል በርካታ ሠራተኞችን ከኢትዮጵያ ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቋን ተናግረዋል፡፡
 
ሳዑዲ እየዘረጋች ያለው አዲስ የአሰራር ስርዓትም ለሠራተኞች የቅጥርና የህክምና ዋስትናን ጨምሮ ደህንነታቸውን የሚያስጠበቅ ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የሥራ ስምሪት ስርዓቱ የተናበበ፣ ዘመናዊ፣ የተገልጋዮችን እንግልት እና ህገ ወጥነትን በሚቀንስ መልኩ በቅርቡ ተግባራዊ እንዲሆን በቅንጅት እንደሚከናወን በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.