Fana: At a Speed of Life!

በፌዴራል ደረጃ ብቻ በሙስና ሊመዘበር የነበረ 753 ሚሊየን ብር ማዳን መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት በፌዴራል ደረጃ ብቻ በሙስና ሊመዘበር የነበረ 753 ሚሊየን ብር ማዳን መቻሉን የፌደራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ ሻሜቦ ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩ ስራዎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ባለፉት ስድስት ወራት በፌዴራል ደረጃ ብቻ በሙስና ሊመዘበር የነበረ 753 ሚሊየን ብር ማዳን መቻሉን አንስተዋል፡፡

በተቋማት የስነ-ምግባር ክትትል ክፍሎች 805 ሚሊየን ብር እና በክልሎች 192 ሚሊየን ብር በድምሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ 998 ሚሊየን ብር ከምዝበራ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም 681 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ማስመለስ መቻሉንም አብራርተዋል።

ሀገር አቀፍ የጸረሙስና ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ 1 ሺህ 608 ጥቆማዎችን ኮሚሽኑ ተቀብሏል ያሉት ስራ አስፈጻሚው÷ ከቀረቡት ጥቆማዎች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት መሬትና መሬት ነክ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በአግልግሎት ዘርፉ ያለው ጥቆማም ከፍተኛ መሆኑን አንስተው÷ ከቀረቡት ጥቆማዎች 250 የሚሆኑት የተፈፀሙ ለመሆናቸው ፍንጭ የተገኘባቸው በመሆኑ የሕግ ሒደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ 692 የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መለየቱን የገለጹት ሃላፊው÷ ከእነዚህ ውስጥ 150 የሚሆኑት ሃብታቸውን ማስመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

ከተመዘገበው ውስጥም ትክክለኛነቱን የማጣራት ስራ የተሰራው በ127ቱ ላይ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.