Fana: At a Speed of Life!

ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አላማን ለማስፈፀም መንቀሳቀስ ተቀባይነት የለውም!

ዘመናትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሰት ግንባታ ሂደት በርካታ የምንኮራባቸውን የአብሮነት፣ የጀግንነት፣ ለጋራ ሀገራዊ ህልውና እና ሉዓለዊነት አብሮ መቆምን፣ አብሮ መዋደቅን በተግባር ያሳየንበትን እሴት ገንብተናል። እነዚህ በጎ ገፅታዎች እስካሁንም በሰፊው ሕዝብ ዘንድ የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል ሆኖ እናገኘዋለን።

በተቃራኒው ብዘሃነትን በአግባቡ አለማስተናገድ፣ ኢትዮጵያ ህብር የብዘሃ ማንነት ባለቤት መሆንዋን የዘነጉ አስተዳደራዊ ሥረዓቶችና ትርክቶች መዘዛቸው እስከ ዛሬም ዋልታ ረገጥ ፅንፈኝነትን ወልደው ብሔራዊ ፈተና ሆነው ይታያሉ። እነኚህ ትርክቶችና አስተዳዳራዊ በደሎች የእኩልነት፣ ነፃነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ከመጫር አልፈው ከፍተኛ ለሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ዳርገውን አላስፈላጊ መስዋዕትነትንም ከፍለንበታል።

ዛሬ እየተመራንበት ያለነው ህገመንግስታዊ ህብረብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥረዓት ለዘመናት መልስ አልባ ሆነው ለእርስ በርስ ጦርነት የዳረጉንን የማንንነት፣ እራስን በራስ የማስተዳደር የሃይማኖት እኩልነት ወዘተ ጥያቄዎችን ህጋዊ እና ህገ መንግስታዊ መሠረት ባለው መልኩ ምላሽ ሰጥቷል።

ምንም እንኳ በፌዴራላዊ ሥረዓታችን ውስጥ የአተገባበር ችግሮች በተለይም ደግም በሀገራዊ እና በብሔር ማንነት መካከል ሚዛን ያለመጠበቅ፣ ጣልቃ ገብነት፣ እውነተኛ ዴሞክራሲ እና ከተቋማት ግንባታ ጋር ክፍተቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብችና ሕዝቦች እራስን በራስ የማሰተዳደር መብት እስከመገንጠል በቋንቋቻው የመጠቀም የመማር በቋንቋቸው የመዳኘት ባህልና ማንነታቸውን የማሳደግ የማበልፀግ እና የሐይማኖት እኩልነት መብታቸውን ተጎናፀፈዋል። እነኚህ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ወደ ኋላ ላይመለሱ ተከባብረውና ተቻችለው አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ቃል ኪዳናቸውን ባፀኑበት ህገ መንግስት ዋስትና አግኝቷል።

ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ደግሞ በፌዴሬሽኑ አተገባበር ሲስተዋሉ የነበሩ የአፈፃፀም ችግሮች በሪፎርም ምላሽ አግኝተዋል። በተለይም አለመግባባትና ሐገራዊ እንድነትን የሚገዳደሩ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦችን ለማረቅ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን ያለፈውን በይቅርታ ዘግተን ለመጪው የጋራ ብልፅግናችን እንደመር በሚል አዲስ ሀገር በቀል አስተሳሰብ በጀመርነው እርምጃ እምርታን ማሳየት ችለናል።

በተለይም ለዘመናት የቆዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስብራቶችን ለመጠገን ዘርፈ ብዙ ለውጦች በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት ማህበራዊ ስብራቶቻችን ለመጠገን የሚረዱ ተቋማትን ህገ-መንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀና በተከተለ መልኩ ለሃይማኖት ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ዓመታት ተለያይተው የቆዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶሶችን በማስታረቅ፤ ፍትሃዊ የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች በመመለስ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የመሬት አቅርቦት በማድረግ ለዘመናት የቆየ የዕምነት ተቋማት ጥያቄን መልሷል፤ በመመለስ ላይም ይገኛል፡፡ ይህ መንግስታዊ ግዴታችን መሆኑን በቅጡ ተረድተን ያደረግነው ስለሆን እንኮራበታለን አጠናክረንም እንቀጥላለን፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ አኩልነትን እንደ በደል የሚያዩ ጥቂት ቆሞ ቀሮች የኢትዮጵያን የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪካዊ ዳራን ያላገናዘቡ አሮጌ ትርክቶችን በማንፀባረቅ ዛሬም እንደ ትላንቱ እኔ ካልወሰንኩልህ በማለት ለራሳቸዉ የሰፉትን ጥብቆ ሁሉንም ለማልበስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህ ሃይሎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የዕምነት አባቶች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ሽፋን በማድረግ እኩይ የፖለቲካ አላማቸውን ለማስፈፀም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሃይማኖት ጭምብል ለብሰው የሚንቀሳቀሱ የድሮ ስርዓት ናፋቂ ቡድኖች ህገ መንግስታዊ ሥረዓትን በሚፃረር መልኩ ሰፊውን ሕዝብ በተለይም ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ ቡድኖች በክልሉ መንግስት በአመራሩና በኦሮሞ ህዝብ ላይ በርካታ የጥላቻና የማጥላላት ዘመቻ ሲያጎርፉ ለሀገረ መንግስቱ አንድነት መፅናት ሲባል በሆደሰፊነት ያለፍን ሲሆን ከዚህ ቦኋላ ህዝባችንም ሆነ የክልሉ መንግስት ትግስቱ ያለቀ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር የፌደራል የፀጥታና ድህንነት የጋራ ግብረ ሃይል ያወጣውን መግለጫ በመደገፍ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመታደግ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ የምንወስድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

ስለሆነም የክልላችን ሰላምና ደህንነት ለማናጋት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በማጋለጥ ህብረተሰቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም

ፊንፊኔ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.