Fana: At a Speed of Life!

ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመው ችግር በሰላማዊ መንገድ፤ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፤ በስክነትና የቤተክርስቲያኗን ውስጣዊ አሰራር በተከተለ መንገድ እንደሚፈታ የክልሉ መንግስት ፅኑ እምነት አለው፡፡

የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድነት ለሀገራዊ ሠላምና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር እጅግ አሰፈላጊ መሆኑን በማመን ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ህገ-መንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀ አኳኋን ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።

የክልሉ ሕዝብ በአብሮነትና ጠንካራ ተሳትፎ በዘላቂነት የቀጠለውን የክልሉን ሰላም ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ ራሱን ከተለያዩ የጥፋት ሃይሎች በመነጠል ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በማድረግ ረገድ ላሳየው የሠላም ባለቤትነት ስሜት የክልሉ መንግሥት ምሥጋናውን ያቀርባል፡፡

በመንግስት በኩል አሁን ላይ በእምነት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዋናነት መፍትሄ የሚያገኙት በራሳቸው በተቋማቱ የውስጥ አሰራር እንደሆነ ሙሉ እምነት አለው፡፡

በመሆኑም በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበና በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ የፓለቲካ ኃይሎች ተቀናጅተው ኢትዮዽያን ለማዳከም ርብርብ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ለመረዳት ተችሏል።

ስለሆነም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄዱና የሀገርና የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅሳቃሴ የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንደሚቃወም ለመግለጽ እንወዳለን።

ክልሉ ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ ማናቸውም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመከላከል፣ በመቆጣጠርና የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ያስተላለፈውን ውሳኔ የመፈፀምና የማስፈፀም ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነቱን ይወጣል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በክልላችን የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችም እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ የተፈጠረው ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የእምነት ልጆቻቸውን በማስተማርና በመገሰጽ የአባትነት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ እየጠየቅን፤ እስካሁን በክልላችን ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለነበረው ጽኑ ፍላጎት የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል።

በዚህ አጋጣሚ ቤተክርስቲያኒቷ የተፈጠረው አለመግባባት በውይይትና ተቀራርቦ በመመካከር እንዲፈታ ለምታደርገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት የተለመደውን ድጋፍ መስጠቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

በሌላ በኩል ፀንቶ የቆየውን የክልሉን ሰላምና ደህንነት በሃይማኖት ሽፋን ወደ አላስፈላጊ ሁከት ለመቀየር የሚደረገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት ፈፅሞ የማይታገስ መሆኑንና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ያለበትን ሃላፊነት በመወጣት የህግ የበላይነትን እንደሚያረጋግጥ ያሳውቃል፡፡

በመጨረሻም የክልሉ መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገ-መንግስታዊ ተግባርና ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅሳቃሴ ሁሉ ሕዝቡ አሁንም ከጎኑ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርደርግ ጥሪውን ያቀርባል።

የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣

የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም

ጋምቤላ፣

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.