Fana: At a Speed of Life!

ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የክልሉ መንግስት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በአገራችን ለውጥ ከመጣ በኋላ ባሉት አመታት መንግስት ህገ መንግስታዊ መርሆዎችን መሰረት በማድረግና በማክበር ዘርፈብዙ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።

የሀይማኖት ተቋማት አንድነትና መጠናከር ለአገራዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ያለውን ፋይዳ በመረዳት በተቋማቱ ውስጥ የነበሩ ልዩነቶች እንዲወገዱም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይታወቃል።

በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባቶች በዋናነት መፍትሄ የሚያገኙት በራሳቸው በተቋማቱ የውስጥ አሰራር እንደሆነ መንግስት በፅኑ ያምናል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው ችግርም የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖና መሰረት ባደረገ ውስጠ ደንብ ሊፈታ ይገባል።

ይሁን እንጂ በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበና በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ የፓለቲካ ኃይሎች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማዳከም ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን በመረጃና በማስረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል።

በመሆኑም ሐይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሀገርና የህዝብ ደህንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ማናቸውንም እንቅሳቃሴ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት አጥብቆ ይቃወማል።

የአገራችንን መልካም ገፅታ ከመገንባት ባሻገር ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ዝግጅት እየተጠናቀቀ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በተገቢው አካል ያልተፈቀደና የደህንነት ስጋት የሚፈጥር የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ማድረግም ተገቢነት ያለው ጉዳይ አይሆንም።

ስለሆነም የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ህገ መንግስቱንና የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ውሳኔን መሰረት በማድረግ ማንኛውንም ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመከላከልና በመቆጣጠር ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ከወዲሁ ያስገነዝባል።

መላው የክልላችን ነዋሪዎችም መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃለፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅሳቃሴ ሁሉ አሰፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ታደርጉ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም
ጅግጅጋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.