Fana: At a Speed of Life!

ወቅታዊ ጉዳይን በተመለከተ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

መንግስት የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድነት ለአገራዊ አንድነትና ግንባታ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህገመንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀ አኳኃን ሰፊ ስራ እየሰራ መቆየቱ የሚታወቅ ነዉ፡፡

በመንግስት በኩል በእምነት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች በዋናነት መፍትሄ የሚያገኙት በራሳቸው በተቋማቱ የውስጥ አሰራር እንደሆነ እና ችግሩ በህገ መንግስታዊ ስርዓት ብቻ የሚፈታ መሆኑን በሚገባ ይረዳል፡፡

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበና በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ የፓለቲካ ኃይሎች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማዳከም ርብርብ እያደረጉ መሆናቸው መንግስት ተገንዝቧል፡፡

በመሆኑም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄዱና የሀገርና የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅሳቃሴ የክልላችን መንግስት የሚቃወም መሆኑን ማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡

ስልጣን በተሰጠው አካል ያልተፈቀደና የደኅንነት ስጋት የሚፈጥር የሕገወጥ ሰልፍ ቅስቀሳ ማድረግ ተገቢነት የሌለው መሆኑ ታዉቆ የክልላችን መንግስት ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ ማናቸውም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን የሚወጣ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

በተጨማሪም በክልላችን የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይልን ውሳኔ የመፈፀምና የማስፈፀም ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነታችሁን እንዲትወጡ እናሳስባለን፡፡

በክልላችን የሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች፤የክልላችን መላዉ ህዝቦችና ሁሉም የፀጥታ አካላት እስካአሁን ከመንግስት ጋር በመሆን በክልላችን ሠላም እንዲሰፍን ላደገሩት አስተዋጽኦ የክልላችን መንግስት ላቀ ያለ ምስጋና ያቀርባል፡፡

የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች፣ምዕመናን እንዲሁም የክልላችን ህዝቦች መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የካቲት 03 ቀን 2015 ዓ.ም
ቦንጋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.