Fana: At a Speed of Life!

በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ከሐረሪ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

ሐረር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) እ.ኤ.አ በ2003/4 በሰላም ፣ በትብብር እና የአብሮነት ከተማነት አለም አቀፍ ሽልማት እና እውቅናን አግኝታለች፡፡
ይህም የተለያዩ እምነት ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት በሰላም፣ በአብሮነት ፣ በመቻቻል በጋራ የኖሩባት እና ዛሬም የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ የተቀዳጀችው ክብር እና እውቅና ነው፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመው ችግር በሰላማዊ መንገድ፤ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፤ በስክነትና የቤተክርስቲያኗን ውስጣዊ አሰራር በተከተለ መንገድ እንደሚፈታ የክልሉ መንግስት ፅኑ እምነት አለው፡፡
ችግሩ ከተፈጠረበት ግዜ ጀምሮ በክልላችን በሐይማኖት ተቋማትና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር እንዳይፈጠር ፍጹም ፍትሃዊ እና ገለልተኛ በመሆነ መልኩ ስንሰራ ቆይተናል።
ሆኖም ግን በሀገራችን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መካከል የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ፍጹም ምዕመናዊ በሆነ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ምእመናኖች እንዳሉ ሆኖ ስውር የፖለቲካ ዓላማቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ኃይሎች እንዳሉ ይስተዋላል።
በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበና በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና የሽብር ሃይሎች ተቀናጅተው ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ይህንን ተከትሎ በሁለቱም ወገን የካቲት 5 ቀን የተጠራው ሰልፍ ለክልሉ ሰላምና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ በመንግስት ያልተፈቀደ እንደሆነ እየገለጸን መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃለፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅሳቃሴ ሁሉ መላው የክልሉ ሕዝብ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደረደርግ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
የሐረሪ ክልላዊ መንግስት
የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም
ሐረር
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.