Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ሚሊየን ዶላር በላይ ያሸሹ ግለሰቦች በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ሚሊየን 97 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር በማሸሽ ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋል የተባሉ አምስት የጉምሩክ ሠራተኞችና ሰባት ነጋዴዎች በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ።

ተከሳሾች በአጠቃላይ 12 ሲሆኑ አምስቱ የጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ ቅርጫፍ ሠራተኛ የሆኑት ግርማይ ደገፋ ጣባ፣ ሜላት መስፍን አበበ፣ እንግዳ አቡ ሞላ፣ ማቲዎስ ካርታ ወታጓ እና ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ጉዳይ በሌላ መዝገብ በሙስና ወንጀል ክስ የተከሰሰው አቶ ወተቱ አበበ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ነጋዴዎቹ ደግሞ ቢኒያም ጌቱ፣ ምስጋናው ካፌ ማርዬ፣ ዮናስ አምሳሉ፣ ተመስገን አራጌ፣ ግርማ ብሩ አንባው፣ ታደሰ በየራ እና ፀጋዬ ኒዳ መሆናቸው በክሱ ተዘርዝሯል፡፡

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ÷ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ በተደራራቢ እና በተናጠል በአጠቃላይ ስምንት ከባድ የሙስና ወንጀል ክሶች አቅርቦባቸዋል።

በክሱ እንደተመላከተው የጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኛ የሆኑት ተከሳሾች በጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ ቅርጫፍ ሲሠሩ በመመሳጠር ከሰባቱ ተከሳሽ ነጋዴዎች ጋር በፈረንጆቹ 2019 እና በ2020 በተለያየ ጊዜ ያቀረቡትን የተለያየ መጠን ያለው አጠቃላይ 1 ሚሊየን 97 ሺህ 100 የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ሀገር ይዘው የመጡት በማስመሰል እና ዲክሌር በማድረግ ሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ በማሳጣት ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

ሰባቱ ነጋዴዎችም በሕገ ወጥ መንገድ አከማችተዋል የተባሉትን ዶላር ከውጭ ሀገር እንዳስገቡት አድርገው በሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ እና ወደ ዳያስፖራ ሒሳብ በማስገባት ከዛም በማውጣት ገንዘቡን ለተለያየ ዓላማ በማዋል መንግስት በበላይነት እና በባለቤትነት የሚያስተዳድረውን የውጭ ምንዛሬ ባማሳጣት በሀገሪቱ ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በሙስና ወንጀል እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብና በመጠቀም ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ዛሬ ረፋድ ላይ በነበረ የችሎት ቀጠሮ ÷ከ 1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች እና 12 ኛ ተከሳሽ በጽሕፈት ቤት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ክሱን ተመልክተው ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ ለየካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.