Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ለጤና ትምህርት ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ አይ ዲ) ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ለሚገኙ 29 የጤና ትምህርት ተቋማት 16 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፉ አምስት የግል ኮሌጆችም ተጠቃሚ ሆነዋል።

በዳግማዊ ምኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተካሄደው መርሐ-ግብር የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ጆናታን ሮዝ ድጋፉን ለተቋማቱ አስረክበዋል።

የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች 300 ሺህ ዶላር ወይም 16 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን፥ ድጋፉ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት ሂደት አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ነው የተገለጸው።

ዩ ኤስ አይ ዲ ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ የሚደግፍ የአምስት ዓመት መርሐ-ግብር እየተገበረ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

መርሐ ግብሩ ከሦስት ዓመት በፊት የተጀመረ ሲሆን እስካሁንም በመርሐ ግብሩ ከ1 ሺህ 380 በላይ የቤተ ሙከራ ቁሳቁስ፣ 13 አውቶቡስ፣ 1 ሺህ 190 ኮምፒውተሮች እንዲሁም ከ12 ሺህ በላይ ጤና ተኮር መጻሕፍትን ከ52 በላይ ለሆኑ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድጋፍ መድረጉ ተጠቁሟል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤፥ የዘላቂ ጤና ግቦች እንዲሳኩ ጥራት ያለው ባለሙያ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው።

የጤና ትምህርት ተደራሽነት ላይ አበረታች ውጤቶች ቢኖሩም ጥራት ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ድጋፉ ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.