Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ 100 ዘመናዊ የከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አውቶብሶችን ስራ አስጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የሚያስችሉ 100 ዘመናዊ የህዝብ ትራንስፖርት አውቶብሶችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች የህዝቡን የትራንስፖር ችግር እና የመንገድ ችግሮችን ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

200 ቀሪ አውቶብሶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚገቡም ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሞትኩ አስማረ በተለይ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር እና ትራንስፖርት ለማግኘት የሚስተዋሉ ረጃጅም ሰልፎችን ለመቅረፍ በእቅድ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

አውቶብሶቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ የተገጠመላቸው ሲሆኑ፥ ለአብነትም መስማት ለተሳናቸው መንገደኞች በምልክት እንዲግባቡ የሚያስችሉ ቴክኖሎጅዎች ተገጥመዋላቸዋል ነው የተባለው።

በተጨማሪም የደህንነት ካሜራ እና መሰል ቴክኖሎጅዎች መኖራቸው ተመላክቷል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ከተማ አስተዳደሩ ያቀረባቸው ዘመናዊ አውቶብሶች በከተማው የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነስ ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ለማዳረስ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

አውቶብሶቹ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ተገልጿል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.