Fana: At a Speed of Life!

ኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲብራራ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፅሁፍ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የማብራሪያው ሙሉ ቃል እንደሚከለው ቀርቧል፦

1) የአዋጁ አስፈላጊነት እና አላማ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ለሃገር እና ለህዝብ አደጋ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሚተዳደርበትን ሥርዓት በአንቀጽ 93 ላይ አስቀምጧል። በአንቀጽ 93 (1) (ሀ) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መነሻ ከሚሆኑ ሁኔታዎች አንዱ “የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት” የሚል ነው። የኮቪድ-19 የሕዝብን ጤንነት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ እንደሆነ ዕሙን ነው።

ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ከተለመደው አሠራር እና ሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፍ ወጥቶ በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይጠይቃል። አዋጁ መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ የተሻለ ነጻነት እና አቅም እንዲኖረው፣ የመንግስት ሥልጣን ላይ ያሉ ገደቦች ወይም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በተለየ ሁኔታ ለጊዜው ተፈጻሚነታቸው ቀርቶ በሙሉ ኃይል፣ በተቀላጠፈ እና በተቀናጀ መልኩ ለወረርሽኙ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በማሰብ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ከሕግ አንጻር አስቻይ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ፤ የዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አላማ፣ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ተግዳሮቶችን በተመለከተ አስፈላጊውን እርምጃዎች የመደንገግ ስልጣን ለስራ አስፈጻሚው የመንግስት አካል መስጠት ነው። እነዚህ አላማዎች ያሉት የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዛሬው እለት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆዋል።

2) የአዋጁ ይዘት

የአዋጁ አንኳር ይዘት በአዋጁ አንቀጽ 4(1) የተገለፀው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወረርሽኙ ሥርጭት እያስከተለ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ለመቀነስ እና ለመከላከል ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚያወጣቸው ደንቦች የመብት እገዳዎችንና፣ እርምጃዎችን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሀ)እና (ለ) መሰረት ለመደንገግ የተሰጠው ስልጣን ነው። ይህም ማለት የወረርሽኙ ሥርጭት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ወይም ለመከላከል እንደሁኔታው እና እንደአስፈላጊነቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማወጣት የመብት እገዳዎችን ማድረግ እና እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል።

እነዚህን የመብት ገደቦች እና እርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያልተቻለው አስፈላጊ የሚሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ከጊዜ ጊዜ እና በሃገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታም ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው። እንደወረርሽኙ ስርጭት የስፋት አድማስ፣ እንደሚያስከትለው ጉዳት አስፈላጊ የሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ሊለዋወጡ ይችላሉ።

አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ ውስጥ ሁሉ የሚያስፈልጉት ክልከላዎች እና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ተለዋዋጭነት ሊኖራቸው ስለሚችል፣ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ በመገምገም እና ስለቫይረሱ ስርጭትም ሆነ ባህሪ የሚገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎችን፣ የህዝብ ጤና ባለሞያዎችን ምክር ከግምት በማስገባት የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስልፈጋል። ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ዝርዝር እና ቋሚ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ከመዘርዘር ይልቅ እንዳስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ (flexible) በሆነ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን እንዲደነግግ አዋጁ ስልጣን ይሰጠዋል። አዋጁ በዚህ መልክ የተቀረፀው አስፈላጊ የሆኑ የመብት እገዳዎች እና እርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ፣ ከቦታ ቦታ ሊለዋወጥ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ ፣ ተጨባጭ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት፣ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ የሆነ እገዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ነው። ይህ አይነት አካሄድ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ እና በሕገ-መንግሥታዊ መብቶችም ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አስፈላጊ ከሆነው መጠን ያላለፈ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል። በደፈናው ከሚጣሉ ገደቦች ይልቅ፣ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ እና ስጋት ከግምት በማስገባት፣ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲህ ያለ ማዕቀፍ ተመራጭ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ደንቦችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማንኛውም ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (4) (ሐ) ልዩ ጥበቃ የተደረገላቸውን ድንጋጌዎች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም። ከዚህ በተጨማሪ በአለም አቀፍ ህግ እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ በተለመደው አሰራር መሰረት ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የ “አስፈላጊነት” እና “ተመጣጣኝነት” መርሆዎችም የሚንስትሮች ምክር ቤትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስልጣን የሚገድቡ አጠቃላይ መርሆዎች ተደርገው በታሳቢነት የሚወሰዱ ናቸው።

• አዋጁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነትን በተመለከት የመብት እገዳዎቹና እርምጃዎቹ ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዚሁ ዓላማ በሚያቋቁመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተወሰነ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ያመላክታል።

• አዋጁ ማንኛውም ሰው በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በሕግ ሥልጣን ባለው አካል የሚሠጥ ሕጋዊ ትዕዛዝ እና መመሪያን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል የሕግ አስከባሪ ተቋማት እና ሌሎች በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ተመጣጣኝ ኃይል በመጠቀም በአዋጁ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ይፋ የተደረጉ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን የማስፈጸም ስልጣን እንደሚኖራቸው ይደነግጋል።

• አንቀጽ 6 በወንጀል ሕግ የተካተቱ አግባብነት ያላቸው የወንጀል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያ ወይም ትዕዛዝን ሆን ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ያስቀምጣል።

• አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ 7 በአቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የሚደነገጉ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎች ዝርዝር ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እና ሕግ የማስረፅ ሃላፊነት በተጣለበት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በስፋት ለሕዝብ ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን መገለጽ እንዳለባቸው ይደነግጋል። የፌደራልም ሆነ የክልል፣ እንዲሁም የግል ሚድያዎች ከዚህ ጋር የሚሰጡ ማብራሪያ እና ገለጻዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለህዝብ የማድረስ ሃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው።

• አዋጁ በመላው ሃገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአምስት ወራት ተፈጻሚ ይሆናል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.