Fana: At a Speed of Life!

በ20 ከተሞች በፀሐይ ኃይል የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ እየተሠራ ነው – የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር በ250 ሚሊየን ብር ወጪ በፀሐይ ኃይል የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማከናወን እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ከተሞች በራሳቸው የመጠጥ ውኃ እንዲያቀርቡ፣ ከውኃ አቅርቦት ታሪፍ ሰብስበው የኢንቨስትመንት ወጪያቸውን እንዲችሉ ቢሮው “የከተሞች የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቶች” በሚል ማዋቀሩ ተገልጿል፡፡

እያንዳንዱ ከተማም በዚሁ መሰረት እደሚሠራ እና ከፍተኛ ወጪ በሚጠይቁ የውኃ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ላይ ግን ቢሮው እገዛ እንደሚያደርግ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንድአጥር መኮንን ተናግረዋል፡፡

የውኃ መሰረተ ልማቶች በኃይል አቅርቦት፣ በኃይል መቆራረጥ እና ወጪ እየተፈተኑ መሆኑን ጠቁመው÷ ችግሩን ለመፍታት በክልሉ የፀሐይ ኃይልን በአማራጭነት አገልግሎት ላይ ማዋል መጀመሩንም አመላክተዋል፡፡

እስካሁን ቆቦ እና ላሊበላ ከተሞች የፀሐይ ኃይልን ለመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት መጠቀም መጀመራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ከተሞች የውኃ አቅርቦቱን ያለማቋራረጥ ማድረስ በመቻሉ ለኤሌክትሪክ አቅርቦት እና ለነዳጅ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረት ብሎም በመቀነስ ረገድ በፀሐይ ኃይል መጠቀሙ ውጤታማ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም በክልሉ የሚገኙ ተጨማሪ 20 ከተሞች በፀሐይ ኃይል ውኃ እንዲያቀርቡ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በክልሉ መንግሥት እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ትብብር የሚሸፈን 250 ሚሊየን ብር ወጪ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

በፀሐይ ኃይል መጠቀሙ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎቶች በየወሩ ለኤሌክትሪክና ነዳጅ ያወጡት የነበረውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለውኃ አቅርቦት ማስፋፊያ እንዲጠቀሙበት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

ክልሉ በ10 ዓመት ዕቅዱ የኃይል አቅርቦትን በፀሐይ እና ንፋስ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለው አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.