Fana: At a Speed of Life!

በግማሽ ዓመቱ የማዕድን ኢንዱስትሪ ምርት የማሳደግ ስራዎች አፈጻጸም 91 በመቶ ተሳክቷል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሥድሥት ወራት የማዕድን ኢንዱስትሪ ምርት የማሳደግ ስራዎች አፈጻጸም 91 በመቶ ማሳካት መቻሉን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
 
ሚኒስቴሩ ባቀረበው የሥድሥት ወራት ሪፖርቱ÷በግማሽ ዓመቱ ትላልቅ ማዕድን አምራቾች የተሰጣቸውን የምርት ፍቃድ ይዞታ በማስጠበቅ የምርት አቅርቦት ማሻሻል እንዲችሉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጿል፡፡
 
ከብረት ማዕድን አንጻር በዘጠኝ ኩባንያዎች 440 ቶን ቁርጥራጭ ብረት ማንሳት የተቻለ ሲሆን፥ በዚህም 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
 
በግማሽ ዓመቱ 88 ነጥብ 9 ቶን ታንታለም እና 1 ሺህ 895 ኪሎ ግራም ወርቅ በኩባንያ እና በባህላዊ አምራቾች መመረቱንም ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
 
በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ጋምቤላ ክልሎች በሕገ-ወጥ የወርቅ ማዕድን ምርት እና ግብይት ሥራ የተሰማሩ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ 26 ግለሰቦችን ለሕግ የማቅረብ ስራ መሰራቱንም ገልጿል።
 
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ቅበላ እንዲጀምር ለማስቻልም ባለሙያዎችን ከመላክ ጀምሮ አስፈላጊው ግብዓት እየተሟላ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
 
በሌላ በኩል ምርትና ምርታማነትን የሚያጎለብቱ ቴክኖሎጂዎችን ለኦሮሚያ፣ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ለጋምቤላ፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለተመረጡ ማህበራት 36 የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ማስተላለፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡
 
በቀጣይ ወርቅ አምራቾች የሚያመርቱትን ምርት ቁጥጥር በማድረግ በአስገዳጅነት እንዲያቀርቡ ማድረግ እና የማያቀርቡት ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አመላክቷል።
 
በክልል በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አመራሮች የሚጠብቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግ ላይም በትኩረት እንደሚሰራ ነው የተጠቆመው፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.