Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ “ለወዳጅ” ሀገራት ነዳጅ የምትልክበትን አቅጣጫ ልትቀይር መሆኑን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ “ለወዳጅ” ሀገራት ነዳጅ የምትልክበትን አቅጣጫ ልትቀይር መሆኑን የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ ተናገሩ፡፡

ሩሲያ በዚህ አመት የዘይት እና የነዳጅ ምርቶቿን ወደ “ወዳጅ” ሀገራት ለመላክ እና አጠቃላይ አቅርቦቱንም ከ75 እስከ 80 በመቶ ከፍ ለማድረግ እንዳሰበች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

የኃይል አቅርቦቱ የዋጋ ተመንን ለሚደግፉ ሀገራት አይደረግም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ረገድ የሀገራቸው አቋም እንደማይለወጥ ተናግረዋል።

ኖቫክ በሀገሪቱ የኃይል ፖሊሲ ላይ ለሚሰራ መፅሔት እንደገለፁት፥ በፈረንጆቹ 2022 የሩሲያ የነዳጅ ምርት 535 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን እንደነበር ጠቅሰው ይህም ከቀደመው ዓመት ምርት ጋር ሲነፃፀር በ 2 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ሩሲያ ለሀገራት የምታቀርበው የነዳጅ ምርት በ7 ነጥብ 6 በመቶ ማለትም ወደ 242 ሚሊየን ቶን መጨመሩንም ነው ሚኒስትሩ የገለፁት፡፡

ባለፈው አመትም “ለወዳጅ” ሀገራት የሩሲያን የነዳጅ ዘይት ለማቅረብ በዋናው ምስራቃዊ የኮዝሚኖ ወደብ በኩል የትራንስፖርት አገልግሎት የማሳደግ ፕሮጀክት መተግበሩንም ጠቅሰዋል።

በዚህ ምክንያት በእስያ-ፓሲፊክ ክልል ውስጥ ላሉ ሀገራት የሚደረገው አቅርቦት በአመት ወደ 42 ሚሊየን ቶን ከፍ ብሏል ማለታቸውን የአር ቲ ዘገባ አመላክቷል።

ሩሲያ ከምዕራባውያን የተጣለባትን ማዕቀብ ተከትሎ የተለያየ የነዳጅ ሽያጭ መንገድ እየተከተለች ትገኛለች።

የአውሮፓ ህብረትም በተጣራ የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን ያወጣ ሲሆን፥ ተመኑም ከፈረንጆቹ የካቲት 5 ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በተመኑ መሰረትም ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ እና ነጭ ጋዝ በበርሜል 100 ዶላር እንዲሁም ሌሎች የነዳጅ ዘይት ምርቶችን በበርሜል በ45 ዶላር የመሸጥ ግዴታ ተጥሎባታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.