Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ እውቅና ለሰጣቸው ታዛቢዎች ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሚያካሂደውን የሕዝበ ውሣኔ ጊዜያዊ ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ እንዲታዘቡ እውቅና ለሰጣቸው ታዛቢ አካላት ጥሪ አቀረበ፡፡

ቦርዱ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ያካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ ጊዜያዊ ውጤት የማመሳከር ሥራ በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላይ አጠናቆ በዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ ጊዜያዊ ውጤቶችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

ቦርዱ የመጨረሻውን ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው የሕዝበ ውሣኔው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መጀመሩን አስታውቋል።

በዚኅም በቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች እና በቦርዱ የዘገባ ፍቃድ የተሰጣቸው የመገናኛ ብዙኃን አካላት እንዲሁም ቦርዱ በድጋሚ ያካሄደውን የቡሌ ምርጫ ውጤት የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ ለመታዘብ ዕውቅና የተሰጣቸው የፓርቲ ወኪሎች በማስተባበሪያ ማዕከሉ በመገኘት የውጤት ማጣራትና ማረጋገጥ ሂደቱን መታዘብ እንደሚችሉ ገልጿል።

ቦርዱ በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የተጣራውንና በቦርዱ የተረጋገጠውን የመጨረሻው የሕዝበ ውሣኔ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ነው ያስታወቀው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.