Fana: At a Speed of Life!

በፌስቡክ ሀሰተኛ ማንነት በማታለል ጾታዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አድርጓል የተባለው ግለሰብ ክሱን እንዲከላከል ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በፌስቡክ ማንነቱን ቀይሮ በመተዋወቅ ‘‘ካናዳ እና እንግሊዝ እወስዳችኋለው’’ በማለት ጾታዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አድርጓል የተባለው ግለሰብ ክሱን እንዲከላከል ብይን ተሰጠ።

ሀሰተኛ ማንነት በመጠቀም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ እና ከ20 ግራም ወርቅ በላይ በመቀበል የግል ተበዳዮቹን ጾታዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አድርጓል የተባለው ተከሳሽ ነው እንዲከላከል ብይን የተሰጠው።

ተከሳሹ ታዲዮስ ዘላለም የሚባል ሲሆን፥ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ነዋሪ ነው።

አራት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በፌስቡክ ነማህበራዊ ትስስር ገጽ ናቲ መላኩ ብሎ ማንነቱን ቀይሮ በካናዳ ነዋሪ በመምሰል ከተዋወቃቸው በኋላ ‘’ካናዳና እንግሊዝ እወስዳችኋለው’’ ብሎ የማታለል ተግባር መፈጸሙ በክሱ ተመላክቷል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ ከካናዳ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ በማስመሰል በግንቦትና በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በተለያዩ ቀናቶች ለአራት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ለሆኑት የግል ተበዳዮች ስልክ ይደውላል፡፡

በዚህም ” ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጉዳይ የሚፈጽምላችሁ ሰው ይመጣል አሻራ የሚወሰደው ከዘር ፈሳሽ እና ከወርቅ ስለሆነ አልጋ ይዛችሁ ጠብቁ በማለት ” የግል ተበዳዮች በተለያየ ቀናቶች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 አልጋ ይዘው እንዲጠብቁ ማድረጉ በክሱ ተዘርዝሯል።

አልጋ እንዲይዙ ካደረገ በኋላ ማንነቱን ቀይሮ ወደ አልጋ ቤት በመሄድ የግብረስጋ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ማድረጉ በክሱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ተከሳሹ ከግል ተበዳይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከእያንዳንዳቸው የተለያየ መጠን ያለው በአጠቃላይ 20 ነጥብ 7 ግራም ወርቅ ለአሻራ ምርመራ ያስፈልጋል ብሎ መውሰዱም ነው በክሱ የተገለጸው፡፡

ለጉዳይ ማስፈጸሚያ በሚል ከእያንዳንዳቸው ግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መቀበሉም በክሱ ተዘርዝሯል።

በተጨማሪም ተከሳሹ ከአራቱ የግል ተበዳዮች መካከል ከአንደኛዋ ተማሪ ለጉዳይ ለማስፈጸም “አይፎን “ሞባይል ስልክ ያስፈልጋል በማለት እንድታመጣ በማዘዝ የስልክ ቀፎውን ለመቀበል በቀጠራት ዕለት ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ በኦፕሬሽን በክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉ በክሱ ተመላክቷል።

በዚህም ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 692/1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በማታለል ወንጀል ተደራራቢ አራት ክሶች ቀርበውበታል።

ተከሳሹ ክሱ ከደረሰውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የቦሌ ምድብ ዓቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዳሉ ያላቸውን የግል ተበዳዮችን ጨምሮ ስድስት ምስክሮችን በችሎት አቅርቦ የምስክርነት ቃላቸውን አሰምቷል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 2ኛ አርቲዲ ወንጀል ችሎት የምስክር ቃል መርምሮ ተከሳሹ ወንጀሉን መፈጸሙ በዐቃቤ ህግ ምስክር ቃል ማረጋገጡን በመግለጽ ተከሳሹ በተከሰሰበት አንቀጽ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሹ መከላከያ ማስረጃ ካለው ለመጠባበቅም ለየካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.